Friday, June 1, 2018

የሶማሌ ልዩ ሐይል እንዲፈርስ አምነስቲ ጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 24/ 2010) በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የሶማሌ ልዩ ሐይልን እንዲያፈርስ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።
ተቋሙ ለጸረ ሽብር በሚል ሰበብ በሶማሌ የተቋቋመው ልዩ ሀይል ፈርሶ በህጋዊ የፖሊስ አባላት እንዲተካም ጠይቋል ።
ልዩ ሃይሉ በሶማሌ መጠነ ሰፊ ጅምላ ግድያና ሰቆቃ በህዝቡ ላይ እየፈጸመ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
የሶማሌ ልዩ ሃይል የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግን/ለመደምሰስ በሚል የተቋቋመ ጦር መሆኑ ይነገራል።
ይህም ሆኖ ግን ልዩ ሃይሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሶማሌ ሕዝብም ሆነ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ግድያና ሰቆቃ እየፈጸመ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ብቻ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉና በሺህ የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገደሉ ልዩ ሃይል ዋናውን ሚና ሲጫወት ነበር።

በሕወሃት የጦር ጄኔራሎች ይታገዛል የሚባለው የሶማሌ ልዩ ሃይል አሁንም መጠነ ሰፊ ጥቃቱን በመቀጠሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድን ጦሩ ከአካባቢው እንዲወጣ ወይንም እንዲፈርስ ጠይቋል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጻ ሰሞኑን ብቻ የሶማሌ ልዩ ሃይል 48 የኦሮሞ ተወላጅ ቤቶችን በማቃጠል ነዋሪዎቹን ወደ ኦሮሚያ እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
እናም የሶማሌ ልዩ ሃይል ፈርሶ አለምአቀፍ ሕግን በሚያከብሩ የፖሊስ አባላት እንዲተካ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቅርቧል።
በተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድና የታላቁ ሃይቅ አካባቢ ዳይሬክተር ጆን ኒያንዩኪ እንዳሉት እነዚህ ጨካኝና ስርአት አልበኛ የሶማሌ ልዩ ሃይል አባላት ሕዝብን እንዲጨርሱ መፈቀድ የለበትም።
ጥቃት አድራሾቹ የሶማሌ ልዩ ሃይል ፖሊስ አባላትም ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳስቧል።
በሶማሌ ክልል እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣም በገለልተኛ አካል እንዲጣራም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment