(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 24/2010) የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ንብረት የሆነው ኤፈርት ከህግ ውጭ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋስትና ከወጭ ሃገር ባንኮች ብድር ሲወስድ መቆየቱ ታወቀ።
ይህንን ሁኔታ በማመቻቸት ለንግድ ባንክ ሃላፊዎች ትዕዛዝ ሲሰጡ የቆዩት የብሄራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ይኽው ህገ ወጥ ድርጊት በመቀጠሉ የኤፈርት ንብረት የሆነው አልመዳ ጨርቃጨርቅ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋስትና መውሰዱ ታውቋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በሚሰጡት ትዕዛዝ ኤፈርት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋስትና ልዩ ልዩ ብድሮችን ከውጭ ሃገራት ለዓመታት ሲወስድ ቆይቷል።
ይህ በዋናነት ለመንግስታዊ ኩባንያዎች ብቻ የሚሰጠው ዋስትና ለኤፈርት ሲሰጥ የቆየው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በሥርዓቱ ውስጥ ባለው የበላይነት እና እንደ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ባሉ ለሕወሃት መሪዎች ታማኝ በሆኑ ግለሰቦች አማካኝነት እንደሆነም ተመልክቷል።
ለብድሩ የሚሰጠው ዋስትና ከኩባንያው ካፒታል ከ5 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት የባንኩ አሰራር ቢያስገድድም ፣ለሕወሃት ኩባንያዎች ለብድሩ መቶ በመቶ ዋስትና ሲሰጥ መቆየቱንም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ይኽው ብድር በመቀጠሉ የአቶ መለስ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ኤፈርትን ከመልቀቃቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ለኤፈርቱ አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ መቶ ሚሊዮን ዶላር ከቻይና ባንክ ብድር ተወስዷል።
ለዚህም እንደተለመደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቶ በመቶ ዋስትና ሰጥቷል።
ኤፈርት የወሰደውን ገንዘብ ወደራሱ አካውንት ያስገባ አያስገባ እንደማይታወቅ እንዲሁም ከብድሩ በፊት የሚያስፈልጉ የብድር ስምምነቶች እንደማይጠየቅም የኢሳት ምንጮች በዝርዝር ይገልጻሉ።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደና ባልተመለሰ 1.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ሕወሃት/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ከተሞችን ሲቆጣጠር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከተለያዩ ተቋማት በተዘረፈ ገንዘብ እና ሃብት መቋቋሙ ይገለጻል።
ኤፈርት በአሁኑ ወቅት እያንዳንዳቸው በቢሊዮን ብሮች ካፒታል የሚንቀሳቀሱ በርካታ ኩባንያዎች ባለቤትም ነው።
የቀድሞው የኤፈርት ሥራ አስፈጻሚ እና የሕወሃት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ከ 5 ዓመት በፊት በሰጡት ቃለምልልስ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በሃብት ኤፈርትን የሚያህል ኩባንያ የለም።
No comments:
Post a Comment