Tuesday, June 5, 2018

መርጌታ እንደስራቸው አግማሴ እንዲፈቱ ተጠየቀ

Image may contain: 1 person, closeup(ኢሳት ዜና ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ በቤትክርስቲያኗ የተክሌ አቋቋም ምስክር ፣ የቤተልሄም ምስክርና ቅኔ መምህር የነበሩት ሊቁ መሪጌታ እንደስራቸው አግማሴ በሃገረ ሰስከታችን በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አግልገሎት ሲሰጡ የቀዩ፣ በጎንደር ከተማም ሃዋርያ ጳውሎስ እየተባለ በሚጠራው የካህናት ማሰልጠኛ በሃገረ ስብከቱ ተመድበው በታሪክ፣ በሂሳብ፣ በመልክዓ ምድርና በዜና መምህርነትና በዚሁም ድርጅት ውስጥ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ማገልገላቸውን፣ በቤተክርስቲያኒቱ ባላቸው እውቀቀትና ስነመግባር በሊቃውንቱ የሚወደዱና መመኪያ የነበሩ ታላቅ ሊቅ መሆናቸውን ይጠቅሳል። እኝህ ሊቅ ከ1986 ዓም ጀምሮ ደብዛቸው የጠፋ መሆኑን የሚገልጸው ደብዳቤው፣ በህይወት የመኖራቸውና ያለመኖራው ጉዳይ ምንም ምላሽ ሳያገኝ ለ24 ዓመታት መቆየቱን ደብዳቤው ይገልጻል። መርጌታ እንደስራቸው ለ24 አመታት በእስር ላይ እንደሚገኙና አሁንም በህይወት እንዳሉ በእስር ቤት ውስጥ ሆነው የላኩዋቸውን ደብዳቤዎች በአስረጅነት በመጥቀስና በህይወት መኖራቸውን የሚገልጹ መረጃዎች ማግኘታቸውን ቤተሰቦቻቸው እንደገለጹለት ሃገረ ስብከቱ በደብዳቤው ገልጿል። የሃገረ ስብከቱ ደብዳቤ መርጌታ
እንደስራቸውን የዚህ ዘመን የቅዱስ ያሬድና የአለቃ ተክሌ ምትክ ናቸው ሲል ያወድሳቸዋል። እኝህ ሊቅ ፍትህ ሳያገኙ ለበርካታ አመታት በእስር ውስጥ መሆናቸው እጅግ የሚያሳዝን ተግባር መሆኑን የጠቀሰው ደብዳቤው ፣ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሊቁን በአፋጣኝ እንዲፈቷቸው ጠይቋል። በአሁኑ ሰዓት የ71 አመት አረጋዊ በመሆናቸው ቀሪ ዘመናቸውንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያሳልፉና ጉባኤ ዘርግተው ተተኪዎችን እንዲያፈሩና የያዙትንም እውቀት ከትውልድ ትውልድ እንዲያሸጋግሩ ጳጳሱ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት በማድረግ የታሰሩበት ቦታ ተጣርቶ ከእስር የሚለቀቁበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ፣ የሊቃውንት መፍለቂያ የሆነቸው ጎንደርም ሊቁን በታላቅ ደስታ ውስጥ ሆና ለመቀበል የተዘጋጀት መሆኑን ገልጿል። መርጌታ እንደስራቸው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት/ ዋና የአስተዳዳር ሰራተኛ ሆነው ሲሰሩ ሃምሌ 12 ቀን 1986 ዓም ጎንደር ላይ ታፍነው ወደ ትግራይ ከተወሰዱ በሁዋላ ያለፉት 24 ዓመታት በእስር አሳልፈዋል። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ለእስር የዳረጋቸው በውጊያ የቆሰለ አንድ የቀድሞ ሰራዊት አዛዥ አሳክመሃል ተብለው መሆኑን ሲጠቅሱ፣ ህወሃት ለመርጌታው አብረዋቸው እንዲሰሩ ጥያቄ እንዳቀረበና እርሳቸው ግን የህወሃትን አገር የመከፋፈል ፖሊሲ በመቃወም አብሬ አልሰራም እንዳሉ ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment