(ኢሳት ዜና ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ/ም) ተወካዩ አቶ ገአስ አህመድ ዛሬ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት ላለፉት 27 ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ክፉኛ የደቀቀው የአፋር ህዝብ እውነተኛ ለውጥ እየጠየቀ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ገዥው የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ -ከህወኃት መሪዎች ጋር በመሆን የህዝብን ጥያቄ በማፈንና ጅምሩን ለውጥ በመቀልበስ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል። ሰሞኑን የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተቃውሞ ሰልፍ ማደረጋቸውን ተከትሎ በትናንትናው ዕለት የአብዴፓ ዋና ጸሀፊ በጉዳዩ ዙሪያም ለማነጋገር የአፋር ወጣቶችን ስብሰባ ቢጠሩም፣ ወጣቶቹ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ባልተገኙበት ሁኔታ ብቻችንን አንሰበሰብም በማለት ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን አቶ ገአስ ተናግረዋል። የወጣቶቹ የለውጥ እየጨመረና ተቃውሞው እየባሰ በመምጣቱ የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በሆኑት በአቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይ የሚመራ ልኡክ ዛሬ መግባቱን የጠቀሱት ተወካዩ፣የጉዟቸው ዓላማ በአብዲ ኢሌ እንደሚመራው ሶህዴፓ ፓርቲ የአፋሩን አብዴፓንም በአቶ አብይ አመራር ላይ ማነሣሳት እንደሆነ የደረሷቸውን መረጃዎች ዋቢ አድርገው ገልጸዋል። እነ ጎበዛይ አብዴፓዎችን “ህወኃት ከሌለ የእናንተም ህልውና የለም” እንደሚሏቸው ያወሱት አቶ ገአስ፣ ልክ መቀሌ ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ “የተሸነፉ ሀሳቦች እያቆጠቆጡ ነው”እንዳሉ ሁሉ ፣ግንቦት 20 በአባላ ከተማ ሲከበርም የአብዴፓው አሊ አብደላ “ደርግ እየተመለሰብን ነው”ብለው ንግግር ማድረጋቸውን አመልክተዋል። ህወኃት የነ አሊ አብደላ የነፍስ አባት መሆኑን የአፋር ህዝብ ያውቃል የሚሉት አቶ ገአስ፣ ሕዝቡ፣ ያነሳው የለውጥ ጥያቄ ከዳር እስኪደርስ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ እንዲሁም አዲሱ የአቶ አብይ አስተዳደር በአፋር አካባቢ በህወኃትና በክልሉ ገዥ ፓርቲ እየፈጸመ ያለውን ደባ እንዲታገሉት ጥሪ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment