(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 24/2010)በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ።
የፌደራል ፖሊስ ወደ ግቢ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን በመደብደብ ጉዳት ማደረሱንም ለማወቅ ተችሏል።
የግለሰቦች ጸብ መነሻ እንደሆነ ቢገለጽም ግጭቱ ወደ እርስ በእርስ ተቀይሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቆም ማድረጉን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
ባለፈው ሳምንት ከግቢው እንዲወጣ በተማሪዎች ተቃውሞ የደረሰበት የፌደራል ፖሊስ የዛሬውን ግጭት ተከትሎ ግቢውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩም ተገልጿል።
ተማሪዎች ከግቢያቸው እንዳይወጡ ተደርገዋል። የታሰሩም እንዳለ እየተነገረ ነው። የዛሬው ግጭት መነሻ የግለሰቦች ጸብ መሆኑን የኢሳት ምንጮች መረጃ ያመለክታል።
በአንዲት የዩኒቨርቲው ሰራተኛና በተማሪ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሰፍቶ ወደ አጠቃላይ ግጭት የተቀየረ መሆኑን ነው ለመረዳት የተቻለው።
የጋምቤላ ዩኒቨርስቲ በማያባራ ግጭት ውስጥ ከገባ አንድ ወር እንደሆነው የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች የግለሰቦች ጸብ ጭምር ወደ ከረረ ግጭት እየተለወጠ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስተጓጉሏል ይላሉ።
በመላ ሀገሪቱ በዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞ በተደረገበት ወቅት በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ጠንካራ እንቅስቃሴ መደረጉን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች መታሰራቸው በዩኒቨርስቲው ተቃውሞ በየጊዜው እንዲከሰት አድርጓል ተብሏል።
የታሰሩት እንዲፈቱ በተማሪዎች በየጊዜው በሚቀርብ ጥያቄና ተቃውሞ የተነሳ በዩኒቨርስቲው መረጋጋት ኖሮ እንዳማያውቅ ይነገራል።
ከሁለት ሳምንት በፊት እንደ አዲስ ያገረሸውን የተማሪዎች ተቃውሞ የምግብ ጥራት ጥያቄ ታክሎበት የተካሄደ ሲሆን የኮማንድ ፖስት ወታደሮች ወደ ግቢው በመዝለቅ ተማሪዎችን ክፉኛ መደብደባቸው ውጥረቱን አባብሶት ቆይቷል።
በወቅቱ 5 ተማሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጅማና መቱ መወሰዳቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ባለፈው ሳምንት የጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በግቢያቸው የሚገኙ የኮማንድ ፖስት ወታደሮች እንዲወጡ በመጠየቅ ዳግም የተቃውሞ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ከዩኒቨርስቲው አስተዳደር ጋር በተደረገ ስምምነት ወታደሮቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።
ከዚህ ቀደም ተማሪዎቹ ተቃውሞ ሲያሰሙ የዩንቨርስቲው አስተዳደር ጥያቄያቸውን ከመመለስ ይልቅ ግቢውን ለቀው እንዲወጡና የምግብ አገልግሎት እንደሚያቋርጥ በመግለጽ ያስፈራራ እንደነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የተማሪው ተቃውሞ የማያቋርጥና በጽናት የቀጠለ መሆኑን ሲገነዘብ በግድም ቢሆን የተማሪውን ጥያቄ መቀበል መጀመሩን ገልጸዋል።
ይሁንና የዛሬውን ግጭት ተከትሎ ግቢውን ለቀው የወጡት የኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ተመለሰው መግባታቸው ታውቋል።
ተማሪዎቹ የታሰሩት ጓደኞቻቸው እንዲፈቱ መጠየቃቸው ተገልጿል። አሁንም በዩኒቨርስቲው ውስጥ የተሰገሰጉ የአገዛዙ ደህንነቶች ተማሪውን እርስ በእርስ ከማጋጨት እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።
ወደ ዩኒቨርስቲው ዘልቆ የገባው የአገዛዙ ሃይል በወሰደው ርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ተመሪዎችም በሆስፒታልና በተለያዩ የህክምና ቦታዎች መወሰዳቸው ታውቋል።
አንዳንድ የመረጃ ምንጮች በግጭቱን የሞት አደጋ መከሰቱን ቢገልጹም ኢሳት ማረጋገጥ አልቻለም።
ውጥረቱ ግን ተባብሶ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment