Thursday, May 31, 2018

የብሔራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መወሰኑን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

(ኢሳት ዲሲ– ግንቦት 23/2010)
ምክትል ገዢው ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በይፋ ከስልጣናቸው መነሳታቸው ታውቋል።
በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ውስጥ የአፍሪካ ሃላፊ አቶ አበበ አዕምሮ ሥላሴ ለብሔራዊ ባንክ ገዢነት መጠየቃቸውም ተሰምቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሃገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ለሁለት ሳምንት ብቻ የሚበቃ መሆኑም ተመልክቷል።
የብሄራዊ ባንክ ገዢዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ የገንዘብ አቅርቦትን በተመለከተ የተዛባ ሪፖርት እንዲወጣ ምክንያት እንደሆኑም ተገልጿል።
እንዲሁም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አልቻሉም በሚል የባንኩ ገዢዎች ከሃላፊነት እንዲነሱ የተወሰነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንበረ ስልጣኑን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ነው።
ምክትል ገዢው ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በዚህ ሳምንት በይፋ ከስልጣን ተነስተው ወደ ሌላ ስፍራ ሲመደቡ፣ዋናው ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በተመሳሳይ እንዲነሱ የተወሰነ ቢሆንም፣ተስፋ የተጣለባቸው ዕጩ ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ሰው እስኪተካ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለጥቂት ሳምንታት በስልጣን ላይ ሊቆዩ እንደሚችሉ መረዳት ተችሏል።

በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ውስጥ የአፍሪካ ሃላፊ በመሆን የሚያገለግሉት አቶ አበበ አዕምሮሥላሴ ለብሄራዊ ባንክ ገዢነት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሳምንታት በፊት የተጠየቁ ሲሆን ዘግይተው በሰጡት ምላሽ የማይችሉበትን ምክንያት አብራርተዋል።
ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በገቡት ውል መሰርት በሥራ እና ስልጣናቸው ላይ መቀጠል ስላለባቸው ጥያቄውን እንዳልተቀበሉት አስታውቀዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢውን የመተካቱ ሥራ አሁንም በተለያዩ አማራጮች መቀጠሉን የሚገልጹት ምንጮች ፣የሃገሪቱ ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ እያቆለቆለ መገኘቱም የባንክ ገዢውን ከመቀየር ባሻገር ኢኮኖሚው ማንሳራራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ የአይ ኤም ኤፍ ድጋፍ መጠየቁም ተሰምቷል፣ ቀደም ሲል ይገለጽ የነበረው ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ አሃዝ የተዛባ እንደነበርም ተመልክቷል።
ለብዙ ጊዜያት የሃገሪቱ ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ ለሰባት ሳምንታት የሚበቃ እንደሆነ ቢገለጽም ፣አሁን በተጨባጭ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለሁለት ሳምንት ብቻ የሚበቃ እንደሆንም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ለተዛባው አሃዝ ዋና ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እና ምክትላቸው ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ምክንያት መሆናቸውም ተመልክቷል።

No comments:

Post a Comment