(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 23/2010) በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ሀና ማርያም በተባለ አካባቢ ቤታቸው የፈረሰባቸው ከ2ሺህ በላይ አባወራዎች በቤተመንግስት አቤቱታ ለማቅረብ ሄደው በፖሊስ መደብደባቸው ተገለጸ።
ትላንት ማምሻውን ወደ ቤተመንግስት ያመሩት የሃና ማርያም ተፈናቃዮች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቤቱታ ለማቅረብ ያደረጉት እንቅስቃሴ በወከባና ድብደባ ተበትኗል።
አቤት የምንልበት ቦታ አጣን በሚል በምሬት የሚገልጹት ተፈናቃዮቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ይድረስልንም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃና ማርያም አካባቢ መኖርያ ቤትን ማፍረስ የተጀመረው ዛሬ አይደለም ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች። ከአንድ መት በፊትም ከ20 ሺ በላይ የሚሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች ያፈናቀ ርምጃ ተወስዷል ሲሉ ያክላሉ።
ያንን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭትም 10 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ያስታውሳሉ። ዛሬም ያ እጣ ፋንታ ለኛ ደርሶናል ይላሉ።ቁጥራቸው 2 ሺ የሚሆነው የሃና ማርያም አካባቢ ነዋሪዎች።
ነዋሪዎቹ ጎጆ ቀልሰው በአካባቢው ኑሮ ከመሰረቱ ከ10 አመት በላይ ማስቆጠሩንም ይናገራሉ።
እነሱ እንደሚሉትም በአካባቢው ኑሯቸውን ሲመሰርቱና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ሲያቀርቡም ሆነ በየቤታቸው ውሃና መብራትን የመሰሉ አገልግሎቶችን ሲጠይቁ የተስተናገዱበት መንገድ ሕጉን የተከተለ እንደሆነም ይገልጻሉ።
እነዚህ ነዋሪዎች ታዲያ ኑሮን መስርተው ንጹህ አየር እየተነፍሱ ባሉበት ወቅት ያለምን ማስጠንቀቂያ ያለምንም ተለዋጭ ቦታ ቤታቸው እላያቸው ላይ እንዲፈርስ ተደርጓል ይላሉ።
ይህን ጉዳይ አቤት ለማለትም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤሮ ጎራ ብለዋል ጆሮውን ግን የሰጣቸው አካል አላገኙም።
መግቢያ አጣን የሚሉት ነዋሪዎች በአካባቢው በላስቲክ ጎጆ ቀልሰው ለማረፍ ያደረጉት ጥረትም በፖሊስ ሃይል እንዲፈርስ ተደርጓል ያላሉ።
በዚህ ከረምት ወዴት ኣንሂድ የሚሉት ነዋሪዎቹ ዛሬ የሰሚ ያለህ ለማለት ወደ ቤተመንግስት ቢያመሩም የገጠማቸው በፖሊስ መደብደብና መዋከብ ነው።
ከቤተመንግስት መልስ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ በመሄድ የጥገኝነት ጥያቄ አቀረብን ያሉት ነዋሪዎቹ እዛም የገጠመን የፖሊስ ዱላ ነው።
እንደ ነዋሪዎቹ አባባል አሁን ላይ እየደረሰባቸው ያለውን ስቃይና እንግልት መንግስት የሚባለው አካል ሊሰማቸው አልቻለም።
እናም ነዋሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይድረስልን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment