(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 6/2010)ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ከአቡነ ማትያስ ጋር በእርቅ ጉዳይ ላይ መነጋገርቸውን አስታወቁ።
በውጭ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ሰላም በሚወርድበት ሁኔታ ላይ ከፓትሪያርኩ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር አብይ አሕመድ የደርግ ባለስልጣናት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ጭምር ይቅርታ አድርገንላቸው በሃገራቸው መኖር ይኖርባቸዋል ማለታቸውም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህንን የተናገሩት ባለፈው ቅዳሜ ከአማራ ክልል ከተለያዩ ዞኖች ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር በቤተመንግስት ባደረጉት ውይይት ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከነሱ ጎን መቆማቸውንም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቅዳሜ ግንቦት 4/2010 ምሽት ላይ በኢዮቤልዩ ቤተመንግስት ከአማራ ክልል ተወላጆች ጋር የውውይት መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብናልፍ አንዱአለምና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን መገኘታቸውን በስፍራው የታደሙ ወገኖች ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አንድነትና ስለይቅርታ ትኩረት ሰጥተው ተናገሩበት በተባለው በዚህ መድረክ ከቀይ ሽብርና ከደርግ መንግስት ጋር በተያያዘ ወደ 23 ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ከሃገር ተሰደው በውጭ እንደሚኖሩ አመልክተዋል።
እነዚህ ኢትዮጵያውያን የቀድሞ መንግስት ፕሬዝዳንት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ጭምር በይቅርታ በሃገራቸው መኖር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ በተለይም ስለውጭው ሲኖዶስ ከፓትሪያርኩ አቡነ ማትያስ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰላም ወርዶ አንድ ጠንካራ ቤተክርስቲያን እንዲኖር ምኞታቸው መሆኑን አመልክተዋል።
ስለይቅርታና ስለአንድነት አጽንኦት በሰጡበት በዚህ መድረክ በተለይ ከአማራ ተወላጆች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በስፋት ተነስተዋል። ባለፉት 27 አመታት አማሮች በአማራነታቸው ግፍና በደል ሲፈጸምባቸው ነበር በማለት አስተያየት የሰጡት ተሰብሳቢዎች በበደል፣በመከፋትና በመገፋት የአማራ ብሔርተኝነት መፈጠሩን አመልክተዋል።
አማሮች በታሪካቸው እንዲያፍሩ መደረጋቸውና ባለፉት 27 አመታት በፖለቲካውና ኢኮኖሚው መገለላቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልልም ሆነ ብአዴን አመራር ጸረ አማራ የሆኑና አማራን የሚጠሉ ግለሰቦች እንዳሉበትም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግዜው የይቅርታና የአንድነት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በእስር ቤት በሚገኙት በሼህ መሃመድ አላሙዲን ጉዳይ ላይ ጭምር ለመነጋገር የፊታችን ሃሙስ ወደ ሳውዳረቢያ እንደሚጓዙም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አቶ ለማ መገርሳ፣አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና እሳቸውን በተመለከተ የሚሰነዘሩ በጎ አስተያየቶች ከኛ ጀርባ ያለውን ደመቀ መኮንን መዘንጋት የለባቸውም ብለዋል ዶክተር አብይ።
No comments:
Post a Comment