(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/ 2010) በአዲስ አበባ በተለምዶ ሃና ማሪያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ መጣላቸውን ገለጹ።
ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ድንገት በአፍራሽ ግብረሃይል ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃችውን አመልክተዋል።
ፋይል በሌላ በኩል የስራ ማቆም አድማ ከመቱ አራተኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩት የቦሌ ለሚ የኢንንዱስትሪ ዞን ሰራተኞች በፌደራል ፖሊስ ሲዋከቡ መዋላቸው ተገልጿል ።
አዲስ አበባ ሃና ማርያም በዳግም መፈናቀልና የነዋሪው ኋይታ ሰሞኑን ውዝግብ ተነስቷል።
3ሺህ የሚጠጉ የሃና ማርያም ነዋሪዎች መውደቂያ ሳይመቻችላቸው በድንገት በተኙበት ቤታቸው ላያቸው ላይ መፍረሱን በምሬት ይገልጻሉ።
ህጋዊ ለመሆናቸው የሚመሰክሩ ማስረጃዎችን ይዘዋል። መብራትና ውሃ በመንግስት በኩል ሲገባላቸው ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ ለመሆኑ የሚያሳዩ ወረቀቶችን ቢያቀርቡም የሚሰማቸው፡ የሚቀበላቸው አላገኙም።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ አስተዳደር ላለፉት 10 ዓመታት ጎጆ ቀልሰው፣ መብራትና ውሃ ሲጠይቁም ተቀብሎ የሞቀ ኑሮ ጀምረው ልጆች ወልደው ቤተሰብ መስርተው ሲኖሩ አንድም ቀን የህጋዊነት ጥያቄ ሳያነሳባቸው ለባለሀብት ቦታው በተፈለገ ጊዜ ድንገት ማፈናቀሉ ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው በማለት ተፈናቃዮቹ ያማርራሉ።
ኢሳት ያነጋገራቸው አንዳንድ ተፈናቃዮች እንደሚናገሩት በአካባቢያቸው ፖሊስ ጣቢያ እንዲያስገነቡ በመንግስት በኩል ተጠይቀው ገንዘብ በማዋጣት የአካባቢያቸውን የፖሊስ ጣቢያ ማስገንባታቸውን የሚገልጹት ተፈናቃዮቹ ይህም ተዘንግቶ እንደ ዕቃ መወርወራችን ትልቅ በድል ነው በማለት ይናገራሉ።
ክፍለከተማው ገንዘባቸውን ወስዶ ፖሊስ ጣቢያውን ሲያስገነባ የህጋዊነት ጥያቄ አላነሳም። ለአንድ ባለሃብት ቦታውን ለመስጠት በሚል ለዓመታት ከኖሩበት እንዲፈናቀሉ ለማድረግ ያለርህራሄ ውሳኔ መስጠቱ በእጅጉን አሳዝኖናል ሲሉም ምሬታቸውን ይገልጻሉ።
ተፈናቃዮቹ እስከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ ለአቤቱታ ሄደዋል። የከንቲባ ድሪባ ኩማን ቢሮ በተደጋጋሚ ደጅ ጠንተዋል።
ጆሮ ሰጥቶ የሚሰማቸው፡ ተቀብሎ የሚያነጋግራቸው አንድም የመንግስት ሃላፊ ግን አላገኙም። የምናደርገው ብናጣ ወረቆቶቻችንን ይዘን ባለሃብቱን ተማጸነው የሚሉት ተፈናቃዮቹ እኔ ምንም ማድረግ አልችልም መንግስትን ጠይቁት እንደተባሉም ይገልጻሉ።
ኢሳት ያነጋገራቸውና ስማቸውን መናገር ያለፈለጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ቅሬታና የሕግ ማስተናገጃ ክፍል ባልደረባ ተፈናቃዮቹ ያቀረቡትን ቅሬታ እየተመለከትነው ነው ሲሉ ምላሽ ሰተዋል።
በሃናማርያምና በአጎራባች አካባቢዎች ባለፈው አመትም በተመሳሳይ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉበት ርምጃ ቁጣን ቀስቅሶ በህዝቡና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ 10 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል አድማ ከመቱ አራተኛ ቀናቸውን የያዙት የቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ዞን ሰራተኞች አሁንም ጥያቄአቸው እንዳልተመለሰ በመግለጽ ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል።
ትላንት በኢሳት ዜናው መቅረቡን ተከትሎ ሰራተኞቹ እየሰሩ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።
አድማውን ለማስቆም በአካባቢው የሰፈረው የፌደራል ፖሊስ ሰራተኞቹን ሲያዋክብ መዋሉ የተገለጸ ሲሆን የተወሰኑ ሰራተኞች ዛሬም መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment