(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 6/2010) የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ከመንግስት ጋር የተናጠል ድርድር ጀመረ።
ቀጣዩን ድርድር በአዲስ አበባ ለማካሄድ የኦዴግ መሪዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ እንደሚገቡም ተገልጿል።
በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ድርድሩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ከመንግስት ከተላኩ ሁለት ልኡካን ጋር መወያየቱን ገልጿል።
የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ እንዳመለከተው ከመንግስት ልኡካን ጋር ድርድሩ የተካሄደው ባለፈው አርብና ቅዳሜ ነበር።
ከኢትዮጵያ መንግስት ሁለት ልኡካን ጋር መነጋገሩን በመግለጫው ያመለከተው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/በሃገሪቱ የሚታዩት የማሻሻያ ርምጃዎች እንዲሰፉ፣እንዲጎለብቱና ጥልቀት እንዲኖራቸው ባለው ፍላጎት ድርድሩ ውስጥ መግባቱን አመልክቷል። እየታየ ባለው የማሻሻያ ርምጃ መበረታታቱንም አስታውቋል።
የተጀመረውን ውይይት ለመቀጠል የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራሮች በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት እንደሚሄዱም ተገልጿል።
ይህም ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚሆንም ተመልክቷል። የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ለለውጥ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያካሂዱም ጥሪ አቅርቧል።
ኦዴግ ከአርበኞች ግንቦት ሰባትና ከሌሎች 2 ድርጅቶች ጋር በፈጠረው ሃገራዊ ንቅናቄ የተናጠል ድርድር እንደማይኖር ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህ የተናጠል ድርድር ከንቅናቄው እውቅና ውጪ መሆኑም ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment