(ኢሳት ዲሲ –ሚያዚያ 24/2010) የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን/ኢሰማኮ/ በአዲሱ የሰራተኛ አዋጅ ላይ ያለውን ቀሬታ በማንሳት ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ እጠራለሁ ሲል አስጠነቀቀ ።
አዲስ የተዘጋጀው የሰራተኛ ረቂቅ አዋጅ ቀድሞ የነበረውን የሰራተኞች መብቶችን የሚያስቀረና ጥቅማጥ ቅማቸውን የሚሳጣ ነውም ብሏል።
የሰራተኛው የደሞዝ ወለል በአዲሱ የሰራተኛና አሰሪ አዋጅ ላይ ይካተት የሚለው ጥያቄም እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱ ሌላ ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ያሉ ሰራተኞች የተለያየ በደል ሲደረስባቸው በተደጋጋሚ ይስተዋላል።
የሚደረስባቸውን በደል ለመከላከል የሚያስችላቸው ህግ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩም ችግራቸው ዘመናት እየተሻገረ ዘልቋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ስራ ድርጅት ኮንፌዴሬሽን 87ትን የፈረመች ቢሆንም የሰራተኛ መደራጀት ላይ ግን ከፍተኛ ችግር መኖሩን የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ተናግረዋል።
ለዚህም የሚያነሱት አስረጂ አዲስ በተገነቡ የኢንደስትሪ ፓርኮች ፣በውጭ ባለሀብቶች የሚተዳደሩ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች መብታቸውን ለማስጠበቅ የመደራጀት መብታቸው መነፈጉን ይጠቅሳሉ።
ሕገ መንግስቱ የመደራጀት መብት ቢሰጥም የኢትዮጵያ ሰራተኞች ግን የመደራጀት መብታቸው ተገድቧል ሲሉም ያክላሉ።
የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኞች አዋጅ መደራጀት የሚፈቀደው ለመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞችና ለግል ድርጅቶች ብቻ መሆኑን ባለሙያዎች ይናግራሉ ። ይህንን ጉዳይም ትክክል ሲሉ የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ባለመቀመጡ ከፍተኛ ችግር የሚደረስባቸው ሰራተኞች ቁጥር በርካታ መሆኑም በተደጋጋሚ ይነሳል።
እነዚህ ሰራተኞች የእለት ጉርሳቸውን እንኳን ለመሸፈን እየተቸገሩ መሆኑን በማገናዘብ መንግስት ይህንን መነሻ ወለል እንዲያስቀምጥ ባለፉት አስር አመታት ቢጠየቅም እስካሁን መልስ መስጠት አለመቻሉ ነው የተገለጸው።
በዚህ ሁኔታ ላይ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ በርካታ መብታቸውን የሚነጥቅና ጥቅማ ጥቅማቸውን የሚነፍግ በመሆኑ መንግስት ሊያነጋግረን ይጋባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሊያ ግን ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ እንጠራለን ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ አነስተኛ የደሞዝ እርከን ባለመኖሩ ቀጣሪዎች ለሰራተኞቻቸው በሚሰሩት ልክ እንደማይከፍሏቸው ተረጋግጧል።
በተመሳሳይ ከውጭ የሚገቡ አሰሪዎችና ባለሀብቶች ከፍተኛ ትርፍ እያጋበሱ ለሰራተኞች በቂ ክፍያ አለመክፈላቸውን ለምን ብሎ የሚጠይቅ አካልና ህግ አለመኖሩም በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
በተጨማሪም አንዳንድ ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ሰራተኛውን ካገናኙ በኋላ ከመሀል መውጣት ሲገባቸው ከሰራተኛው ላይ ደሞዝ እየቀነሱም እንደሚወስዱ መራጃዎች ያሳያሉ ።
በአሰሪና ሰራተኛው መካከል ችግር ሲፈጠር ግን እነዚህ አገናኞች ደብዛቸው እንደሚጠፋ በዚህም ሳቢያ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚደርስ ችግሩ የደረሰባቸው አካላት ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment