(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2010) በብራስልስ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው በቅርቡ ተሹመው የነበሩት አቶ እውነቱ ብላታ ከሃላፊነታቸው ተነሱ።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ምክንያቶች የአምባሳደሮች ጥሪና ሽግሽግ ማካሄዱን አስታወቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎም በሪያድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተነስተው በሌላ እንዲተኩ መደረጉ ተሰምቷል።
ወይዘሮ አስቴር ማሞና አቶ እውነቱ ብላታ ከእነ ባለቤቶቻቸው በአንድ ኤምባሲ እንዲሰሩ መመደባቸውም ጥያቄ አስነስቷል።
ይህንኑ ተከትሎም በብራስልስ የኢፌድሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው በቅርቡ ተሹመው የነበሩት አቶ እውነቱ ብላታ ከሀላፊነታቸው ተነስተዋል። በተያያዘ ዜናም አምባሳደር አሚን አቡዱል ቃድር ከሪያድ ወደ አልጄሪያ ተዛውረው ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ተመድበዋል።
አምባሳደር ውብሸት ደምሴ ደግሞ ከጅዳ ቆንስላ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተጠርተዋል።
በአልጄሪያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሰለሞን አበበ ወደ ናይጄሪያ እንዲሁም አምባሳደር ግሩም አባይ ከሞስኮ ወደ ብራስልስ የኢፌድሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው በተመሳሳይ ኃላፊነት ተዛውረዋል።
አምባሳደር አብዱላዚዝ አህመድ ከኩዌት የኢፌድሪ ኤምባሲ ወደ ሪያድ የኢፌድሪ ኤምባሲ ተዛውረዋል።
ሰሞኑን በነበረው ሁኔታ ከኃላፊነት የሚነሱ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአምባሳደርነት የሚሾሙበት አሠራር በፓርላማ ጥያቄ አስነስቷል።
በፓርላማው የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከኃላፊነት የሚነሱ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብቃትና ልምድ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ በአምባሳደርነት መመደባቸው የሃገርን ጥቅምና ገጽታ እየጎዳ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የአምባሳደሮቹ ምደባ በትምህርትና በብቃት ላይ ተመሥርቶ እንዲስተካከል ይደረጋል ብለዋል።
No comments:
Post a Comment