Wednesday, May 30, 2018

የፌደራል ፖሊስ ሶስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ተነሱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 22/2010) የፌደራል ፖሊስ ሶስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ከስልጣን ተነሱ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ወደ ፌደራል ፖሊስ ሲዛወሩ፣ የቤተመንግስት አስተዳደር ሃላፊም ተሽረው ፣በምትካቸው አዲስ ሃላፊ ተሹሟል።
ከሁለት ዓመት በፊት ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ሃላፊነት የተባረሩት ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ የአንድ ኤጀንሲ ሃላፊ ሆነው መሾማቸውም ታውቋል።
በአዲስ አበባ የሚታተመው ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ አዲስ ፎርቹን እንደዘገበው በፌደራል ፖሊስ ውስጥ ለረጅም አመታት የወንጀል መከላከል ሃላፊ በመሆን ሲሰሩ የቆዩትና በተግባር እውነተኛው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ሃላፊ ተደርገው የሚጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ግርማይ ከበደ ወይንም ግርማይ ማንጁስ ተነስተው በምትካቸው መላኩ ፈንታ ተሹመዋል።
መላኩ ፈንታ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩ መሆናቸውም በዘገባው ላይ ተመልክቷል። በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ የወንጀል ምርመራ ዋና ሃላፊ ረታ ተስፋዬ ተነስተው በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሃላፊንት ላይ የነበሩት ተኮላ አይፎክሩ ተሹመዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይህደጎ ስዩም ወደ ፌደራል ፖሊስ ተዛውረው የሰው ሃብት ክፍል ሃላፊነቱን ወስደዋል።
በዚህ የሃላፊነት ስፍራ ላይ የነበሩት ሲሳይ ሽኩር ከስልጣናቸው ተነስተዋል። ከ20 አመታት በላይ የቤተመንግስት ዋና ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ገብረትንሳኤ ገብረሚካኤል ከስልጣናቸው ተወግደው በምትካቸው ወርቅነሽ ብሩ የሚባሉ ሰው ተተክተዋል።
ወርቅነሽ ብሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩ ናቸው። የተሸኙት ገብረትንሳኤ ገብረሚካኤል የሕወሃት ታጋይ የነበሩ ሲሆኑ ከቤተመንግስት ሃላፊነት በፊት የአቶ መለስ ረዳት ነበሩ።
የቤተመንግስት አስተዳደር በሃገሪቱ የሚገኙ 13 ቤተመንግስቶችን በበላይነት የሚቆጣጠር መሆኑም ተመልክቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩትና ከ2 አመት በፊት ከዚህ የሃላፊነት ቦታ የተባረሩት የሕወሃቱ ታጋይ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ የብሔራዊ ኩነቶች መመዝገቢያ ኤጀንሲ ሃላፊ ሆነው ከግንቦት 9/2010 ጀምሮ መሾማቸው በዘገባው ተመልክቷል።
ቀደም ሲል የፌደራል ፖሊስ ዳይሬክተር ጄኔራል የነበሩት አቶ አሰፋ አብዩ በአቶ ያሬድ ጥላሁን ተተክተዋል።
ሁለቱም የደኢህዴን አባላት ናቸው። አቶ አሰፋ አብዩ የሃገሪቱ የፌደራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ተብለው ቢቀመጡም ስልጣኑ አሁን ከሃላፊነት በተነሱት የወንጀል መከላከል ሃላፊው ኮሚሽነር ግርማይ ከበደ ወይንም ግርማይ ማንጁስ እጅ እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን እንደወጡ በከፍተኛ የሃገር ሃብት ምዝበራ የሚጠቀሰው ተቋም ሜቴክ ዋና ሃላፊን የሕወሃቱን ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን በዶክተር በቀለ ቡላዶ መተካታቸው ይታወሳል።
የሃገሪቱ የሳይበር ስለላ ተቋም ዳይሬክተር ጄኔራል ተኮላ ብርሃን ወልደ አረጋይና ምክትላቸው በተመሳሳይ ከስልጣን ተነስተዋል። ሶስቱም የሕወሃት ታጋዮች ናቸው።

No comments:

Post a Comment