ሳምንታዊ ርእሰ አንቀፅ
ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ አገዛዝ ለሩብ ምዕተ አመት ሲያራምደው የኖረው የብሄር ፖለቲካን ተከትሎ በርካታ ዜጎች በብሄር ማንነታቸው ብቻ እንደባዕድ እየተቆጥሩ ለበርካታ አመታት ከኖሩበትና ጥረው ግረው ንብረት ካፈሩበት የአገራቸው ክፍል ሲፈናቀሉ፤ ሲሰደዱና ሲገደሉ ኖረዋል። በዚህ የማፈናቀል ዘመቻ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግንባር ቀደም ተጠቂ ሆኖ የቆየው ህወሃት ከምስረታው ጀምሮ በጠላትነት የፈርጀው የአማራ ማህበረሰብ አባላት እንደሆኑ ግልጽ ነው።
አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ዕለት ጀምረው ህወሃት በግልጽ ሲያራምደው ከኖረው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲና የድርጅታቸው ፖለቲካ አቋም ወጣ ባለ በሚመስል መልኩ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራትና የመኖር ነጻነት እንዳለው በይፋ እየተናገሩ ያለ ቢሆንም ዜግችን በብሄረሰብ ማንነታቸው ምክንያት ከተለይዩ ቦታዎች የማፈናቀል ዘመቻ ገደብ ሊበጅለት እንዳልቻለ በተግባር እየታየ ነው። ሰሞኑን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሃብት ንብረታቸውን ተቀምተው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ከ150 በላይ የአማራ ተወላጆች ጉዳይ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሃቅ ነው።
ዜጎች በፈለጉት የአገሪቱ ግዛት ተዘዋውረው የመሥራትና የመኖር ነጻነት በጠቅላይ ሚንስትሩ አንደበት ጭምር ጎላ ብሎ እየተነገር ባለበት በዚህ በአሁኑ ወቅት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ በክልሉ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ለማባረር ድፍረት ያገኘው በህዝብ መካከል ጥላቻንና ግጭትን በመፍጠር ስልጣን ላይ ተደላድሎ ለመቀጠል ሌት ተቀን እየማሰነ ያለው የህወሃት አገዛዝ አይዞ ባይነት ታክሎበት እንደሆነ መገመት አያስቸግርም። ምክንያቱም በተቀነባበረ ተመሳሳይ ሴራ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የኦሮሞ ተወላጆች ከሱማሌ ክልል ሲፈናቀሉ ታይቶአልና። እናም በአማራው ወገናችን የሚደርሰው መፈናቅል፣ ግድያና እስራት መቀጠሉ የህወሃት ለአማራው ያለውን የከፋፍለህ አጀንዳ ፖሊሲ ያየነበት አሳዛኝ ድርጊት ነው።
ህወሃት የዜጎች መፈናቀል ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያደረገ ያለው ለ27 አመት የዘለቀው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዙ እንዲያበቃ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ትግል በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ጭምር የበላይነቱን የሚግደራደር የለውጥ ሃይል ስለፈጠረበት በለመደው ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ስልቱ እነዚህን የለውጥ ሃይሎች በማዳከም እንደገና መልሶ ለማንሰራራት ያስችለኛል በሚል የፖለቲካ ሰሌት ነው። ከኢህአደግ ውስጥ ብቅ ብቅ እያለ ያለው ይህ የለውጥ ሃይል ለአመታት የተጫነበትን የበታቸኝነትና በራስ ያለመተማመን ስሜት ሰብሮ በመውጣት በየአደባባዩ ለህዝብ እየሰጠ ያለው የለውጥ ተስፋ በተግባር የማይገለጽ መሆኑን ለማሳየት ስለፍቅር ሲናገር ጥላቻን ፤ ስለህዝብ አንድነት ሲናገር ክፍፍልን አጠናክሮ መቀጠል ለህወሃት የቀረው ብቸኛ የመጫወቻ ካርድ ሆኖአል።
ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ህወሃት ከበስተጀርባው ሆኖ በሚሸርበው ተንኮል ተነሳስተውም ሆነ በራሳቸው ኋላ ቀር አስተሳሰብ በክልላቸው ውስጥ በሠላም ሠርተው የሚኖሩትን የአማራና ሌላ ብሄረሰብ አባላት የሚያፈናቅሉ ክልል መሪዎች በዜጎቻችን ላይ የሚፈጽሙትን ወንጀል አጥብቆ ይቃወማል። የአማራን ክልል እያስተዳደረ ያለው ብአዴንም ዘራፊው የህወሃት አመራር በህዝባችን ላይ እስከዛሬ ሲፈጽም የኖረውን ወንጀል በዝምታ ከመመልከት እራሱን አላቆ ኦህዴድ አቻው በህወሃት ሴራ ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ያደረገውን አይነት መጠለያ የመስጠትና መልሶ የማቋቋም እርምጃ በአፋጣኝ በመውሰድ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተባረው ወደ ክልሉ የመጡትን ወገኖቻችንን በአስቸኳይ እንዲታደግ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ህወሃት ምንም አይነት ወገናዊም ሆነ አገራዊ ፍቅር በሌላቸው የሃብት ዘረፋን የመጨረሻ ግብ አድርገው በሚንቀሳቀሱ ወንጀለኞችና ራስ ወዳዶች የተሞላ ድርጅት መሆኑ ዛሬ ከምንግዜውም በላይ ግልጽ ሆኖአል። በዚህም የተነሳ እስከዛሬ በጉልበት ይዞት የኖረው ፈላጭ ቆራጭነቱን ብቻ ሳይሆን አገር የማስተዳደር ህጋዊነቱንም አጥቶአል። ይህንን መረዳት የተሳናቸው በጥቅም የታወሩ አንዳንድ የኢህአዴግ እና የአጋር ድርጅቶቹ አመራሮች የአገዛዝ ዕድሜው እያከተመ ከመጣው ከዚህ የህወሃት ቡድን ጋር በመወገን በህዝባችን ላይ እያደረሱ ላሉት ዜጎችን ማፈናቀል፤ ማሰርና መግደል ወንጀል በህግና በታሪክ ፊት ተጠያቂ የሚሆኑበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን አውቀው ከተግባራቸው እንዲታቀቡ አርበኞች ግንቦት 7 ያስጠነቅቃል።
ህዝባችን ላለፉት 27 አመታት ሲፈጸምበት ከኖረውና እየተፈጸመበት ካለው ከዚህ የመፈናቀል፤ የስደትና ግድያ ህይወት መላቀቅ የሚችለው ህወሃት ለከፋፍለህ ግዛ አላማው በመላው አገራችን የዘረጋው የፖለቲካና የአስተዳደር መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ ሲቀየርና በነጻና ገለልተኛ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስርአት በአገራችን ሲሰፍን ብቻ እንደሆነ አውቆ ትግሉን በተለያየ ፈርጅ እያካሄደ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሃት /ኢህአደግ ውስጥ የተፈጠሩትና ህዝብ በተወሰነ ደረጃ ድጋፉን እየሰጣቸው ያሉት የለውጥ ሃይሎችም ከህዝባችንና ለዲሞክራሲ ከምንታገል የአገሪቱ ዜጎች ጎን በመሰለፍ ይህንን የዘመናት ስቃይና መከራ የማስቆም ሃላፊነት መወጣት ወቅቱ የጣለባቸው የታሪክና የዜግነት ግዴታ መሆኑን እንዲረዱ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ህዝባችን ላለፉት 27 አመታት ሲፈጸምበት ከኖረውና እየተፈጸመበት ካለው ከዚህ የመፈናቀል፤ የስደትና ግድያ ህይወት መላቀቅ የሚችለው ህወሃት ለከፋፍለህ ግዛ አላማው በመላው አገራችን የዘረጋው የፖለቲካና የአስተዳደር መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ ሲቀየርና በነጻና ገለልተኛ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስርአት በአገራችን ሲሰፍን ብቻ እንደሆነ አውቆ ትግሉን በተለያየ ፈርጅ እያካሄደ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሃት /ኢህአደግ ውስጥ የተፈጠሩትና ህዝብ በተወሰነ ደረጃ ድጋፉን እየሰጣቸው ያሉት የለውጥ ሃይሎችም ከህዝባችንና ለዲሞክራሲ ከምንታገል የአገሪቱ ዜጎች ጎን በመሰለፍ ይህንን የዘመናት ስቃይና መከራ የማስቆም ሃላፊነት መወጣት ወቅቱ የጣለባቸው የታሪክና የዜግነት ግዴታ መሆኑን እንዲረዱ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
እስር ፤ ግድያ፤ መፈናቀልና መሰደድ ከአገራችን ምድር ጨርሶ የሚጠፋው ህወሃት /ኢህአዴግ የመጨረሻው አምባገነን ሥርአት ሆኖ እንዲያልፍ መላው ህዝባችን በተለይም የነገው አገር ተረካቢው ወጣት እየተካሄደ ያለው ትግል በድል እስኪቋጭ ድረስ ተባብሮና ተጣምሮ ሲገፋው ብቻ እንደሆነ ሁሉም እንዲገነዘብ እርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment