Friday, January 1, 2016

“የአዲስ አበባ ማስትተር ፕላን አልቆመም በሱሉልታ የመሬት ቅርምቱ ቅጥሏል” ይላሉ የሱሉልታ ነዋሪዎች።


ከመቶ ለሚበልጡ የኦሮሞ ተወላጆች ሞት ምክንያት የሆነዉ፣ አያሌ የኦሮሞ ተወላጆች ታስረዉ ለስቃይ አያያዝ የተጋለጡበት፣ እዉቅ የፖለቲካ መሪዎች፣ጋዜጠኞች፣ የሲቪክ ተቋማት አገልጋዮች ታፍነዉ የተወሰዱበት፣ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የፈሰሰበት ደም ሳይደርቅ መመሪያዉ ወደ መሬት እየወረደ ነው ሲሉ የሱልልታ ነዋሪዎች ለቢቢኤን ገለጹ።
የሱሉልታ ማዘጋጃ ቤት የገበሬዉን መሬት ለመንጠቅ ማስትወቂያ አዉጥቷል የሚሉት ነዋሪዎች፤ የማዘጋጃቤት ሰራተኞች በድምጽ ማጉያ መሬት መዉሰድ የሚፈልግ ካለ መመዝገብ ይችላል በማለት በየመንደሩ እይዞሩ ማስተዋወቅ መጀመራቸዉንም ይገልጻሉ።
በአካባቢው ያለዉ ገበሬ ወደ ‘መሬት ለመተግበር የመጣ መመሪያ የለም’ በማለት የእርሻ ስራዉን ከመቀጠል በስተቀር ጉዳዩን እምብዛም በጥልቀት ያለተመለከተዉ መሆኑን የሚገልጹት የሱሉልታ ነዋሪዎች፤ የከተማዉ ህዝብ ‘እንጫረሳታለን እንጂ መሬታች አይወሰድም’ በሚል የትግል መንፈስ ዉስጥ መሆኑን ጨምረዉ ለቢቢኤን ገልጸዋል።
ሱሉልታ በፌደራል ፖሊስ እንደተከበበች የሚገልጹት የሱልልታ ነዋሪዎች፤ የማዘጋጃ ቤት ሰራተኞች የመሬት ጫረታ ማስታወቂያን መለጠፋቸዉና በየመደሩ እየዞሩ ለመሬት ጫረታ በድምጽ ማጉያ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑ ታዉቋል።ይህም በአካባቢዉ ያሉ የኦሮሞንና የአማራን ብሎም የሌላ ብሔር ተወላጆችን ለማጋጨት ሆን ተብሎ የሚደረግ ሴራ በመሆኑ፤በዚህ ጫረታ ዉስጥ ባለመሳተፍ የሱሉልታ ነዋሪዎች ቁርጠኝነትን ሊያሳዩ ይገባል በማለትም ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የሳተላይት ዲሽ በግዳጅ መነቀሉን ያስታወሱት ነዋሪዎች፤ የበርካታ ሰዎች ዲሽ ተዘርፎና ተሰባብሮ ባለበት መልኩ ዳግም ዲሽ ስቀሉ የሚል የፖሊሶች ግፊት መኖሩን ይገልጻሉ።
በህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ የሚመራዉ መንግስት ባንሰራፋዉ ብሔራዊ ጭቆና ዜጎችን እያጠቃ በመሆኑ በሱሉልታም ይሁን በሌላ አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ጠንክረዉ በጋራ መስራት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል። የኦሮሞና የአማራን ህዝብ ለማጋጨት መንግስት የተቻለዉን ሁሉ እያደረገ መሆኑን የሚገልጹት የሱሉልታ ነዋሪዎች እነዚህ ለአያሌ አመታት ተጋብተዉና ተዋልደዉ የኖሩ ህዝቦች የበለጠ ግንኙነታቸዉን አጠናክረዉ ይህንን በአገራችን ላይ የመጣዉን ፈተና በመቋቋም ኢትዮጵያን ሊታደጓት ይገባል ብለዋል።
“የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ቆሟል፤ ከህዝባችን ፍላጎት ዉጪ ሊከሰት የሚችል ነገር የለም!” በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ቢናገሩም፤ በሌሎች የኦሮሚያ ቦታዎች ተቃዉሞዎች እየተደረጉ፣ሰዎች እየታሰሩ፣ የተደበደቡና በጥይት የቆሰሉ በሞትና በህይወት መካከል ባሉበት ሰዓት፤ ሱሉልታ ለጨረታ ቀርባለች ገብሬዉ የእርሻ መሬቱን የማጣትና የመፈናቀል እጣ ከፊት ለፊቱ መደቀኑን የሱሉልታ ነዋሪዎች ለቢቢኤን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment