(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 26/2010)በኢትዮጵያ እና በሱዳን አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ግጭት መፈጠሩ ተሰማ።
የግጭቱ መንስኤ የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የኢትዮጵያን የእርሻ መሬት እንዳያርሱ በመከልከላቸዉ ነዉ ተብሏል ፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እና በሱዳን የጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት ተከስቷል፡፡
ከሱዳን ጦር ጋር አብረው ወጊያውን የቀሰቀሱት የሕወሐት ሰዎች መሆናቸውን የአይን እማኞች አረጋግጠዋል።
ለግጭቱ መንስኤ የሆነውን የእርሻ መሬት ለረጅም ዓመታት እየተጠቀሙበት የሚገኙት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ናቸዉ፡፡
አሁን ግን የሱዳን አመራሮች ‹‹የእርሻ መሬቱን መጠቀም ያለብን እኛ ነን›› የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ሃሳቡ ተገቢነት የሌለዉ መሆኑንም ለአካባቢዉ የሱዳን አመራሮች አስረድተናል ብለዋል። የሱዳን አመራሮች ግን ሃሳቡን ባለመቀበላቸዉ መግባባት እንዳልተቻለ ነዉ የገለጹት።
ግጭቱ የተከሰተዉ በመተማ ወረዳ ደለሎ ቁጥር 4 የእርሻ እና የኢንቨስትመንት ቦታ እና በሱዳን ባሶንዳ ዞን መካከል በሚገኝ ቦታ ነዉ፡፡
በዚህም ከሁለቱም በኩል ህይዎታቸዉን ያጡ እና የቆሰሉ መኖራቸዉን ሰምተናል፡፡ ግጭቱን ለማረጋጋት የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢዉ ተሰማርተዋል፡፡
የአይን እማኞች እንደሚሉት ደግሞ ተኬ በተባለ የሕወሐት የአንድ ዞን የፀጥታ ሀላፊ አስተባባሪነት በሱዳን በኩል በተደረገ ዝግጅት በሶስት አቅጣጫ ጦርነት ተጀምሯል።
በቋራ፣ በመተማ ቁጥር አንድ እና በጓንግ በኩል የታቀደው ጦርነት በዚሁ አካባቢ ተጀምሯል። በቋራ በኩል የአማራ ገበሬዎች አንድ የሱዳን ፓትሮልን መማረክ ሲችሉ፣ በመተማ በኩል የተከፈተ ጦርነት የብዙ ገበሬዎችን ህይወት ቀጥፏል።
በጓንግ በኩል ገበሬዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀም የተዘጋጀ የሱዳን ጦር እንዳለ ታውቋል። በአማራ ገበሬዎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ያለው የሱዳን ሰራዊት ከባድ መሳርያ የታጠቀ ሲሆን ገበሬዎቹ ያዙት አጭር ርቀት መሳርያ ነው።
በመሆኑም የክልሉ ልዩ ሀይል እገዛ እንዲያደርግላቸው፣ እገዛ ካላደረገም የረዥም ርቀት መሳርያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ተብሏል።
በዛሬው ጦርነት የቆሰሉ ገበሬዎች እና የልዩ ሀይል አባላት በጦርነቱ ከሱዳን ጦር በተጨማሪ “ኢትዮጵያውያንም” አሉበት ሲሉ የኢሳት ምንጮች ተናግረዋል።
“የወጋን ሕወሓትም ጭምር ነው ሲሉ አክለዋል ለመረጃ ምንጮቹ። እንደ መረጃ ምንጮቹ ከሆነ በአካባቢው የተኩስ ልውውጡ አሁንም መኖሩን ተከትሎ የቆሰሉትን ወገኖችን መታደግም ሆነ የሞቱትን አስከሬን ማንሳት አልተቻለም።
No comments:
Post a Comment