(ኢሳት ዲሲ– ሰኔ 26/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ እንዲሁም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በባህርዳር የፋሺዝም ተግባር አሳይተዋል ሲሉ የቀድሞው የኢንሳ ዳይሬክተር ገለጹ።
የሕወሃቱ ነባር ታጋይ እና የቀድሞው የኢንሳ ዳይሬክተር ሜ/ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ በዚህ አካሄድ ከማንም ጋር የመኖራችን ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።
ትናንት ከትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ ብአዴን እና ኦህዴድ አንድ የሆኑት ሕውሐትን ለማጥፋት ነው ብለዋል።
ሆኖም መልሰው ራሳቸው ይፋጃሉ ሲሉም ተደምጠዋል። ትናንት ምሽት በትግራይ ክልል ቴሊቪዥን አቶ ገብረመድህን ገብረ ሚካኤል ከተባሉ መምህር ጋር ቀርበው በውቅታዊ ጉዳዮች ውይይት ያደረጉት ሜ/ጄነራል ተ/ብርሃን ወልደ አረጋይ “…ዓብይ አዲስ አበባ ላይ ፣ገዱ ባህር ዳር ላይ የቀን ጅብ የሚል ቃል ተጠቅመዋል። ይህ ፋሽዝም ነው። ….” በማለት ገልጸዋል ።
”አብይ አሸባሪዎችን ከውጭ ሃገር ጠርቷል፣ከእስር ቤትም ፈቷል ። ይህ ኢ ሕገመንግስታዊ ነው “ በማለት የእስረኞችን መፈታት ጭምር የተቃወሙት ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አካሄድ በሙሉ ሕገወጥ እንደሆነም አመልክተዋል።
ለ 9 ዓመታት ያህል በውህኒ ቆይተው የተፈቱት ጄነራል አሳምነው ጽጌ ባህርዳር ላይ ዶ/ር አብይን ማወዳሳቸውን የተቃወሙትና ይህን ወዳሴ የሚያቀርበው ክእስር ሰላስፈታው ነው በማለት የተናገሩት ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ “ሰውየው ጀግናም እየተባለ ነው” በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርበው ሙገሳ እና ወዳሴ እንዳላስደሰታቸው አሳይተዋል።
“የአሁኖቹ አመራሮች የ97ቱ ጋዜጦችና መፅሔቶች ውጤቶች ናቸው” በማለት አዲሶቹን አመራሮች የገለጹት ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ‘ኦህዴድና ብአዴን ህወሀትን ለማጥፋት ነው አንድ የሆኑት እንጂ በኋላ ላይ ይፋጃሉ።
ዓላማቸው ትግራይን በሠሜን በሻዕቢያ በደቡብ ደግሞ ሁለቱ አጣብቀው ማንበርከክ ነው የፈለገት ” በማለት ተናግረዋል።
ሲቀጥሉም “የትግራይ ህዝብ ግን እንደማይንበረከክ ሊያቁት ይገባል።ህወሀትና የትግራይ ህዝብ የተዋሀዱት በኬሚስትሪ ውህደት ነው።
ህወሀት ያልሆነ ትገሬ የለም። ሁሉም ትገረዋይ ህወሀት ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ጄነራሉ በወልቃይት እና በራያ ተወላጆች የሚነሱ ጥያቄዎችንም የጦርነት አዋጅ ነው ሲሉ ገልጸዋል። “…ራያ ወልቃይት የሚባሉትን መጠየቅ ጦርነት በኛ ላይ እንደማወጅ ይቆጠራል።
ልክ ሱዳኖች የኢትዮጵያን መሬት እንውሰድ እንደሚሉት።>> የሕወሃቱ ነባር ታጋይ እና የቀድሞው የኢንሳ ዳይሬክተር ሜ/ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ በዚህ አካሄድ ከማንም ጋር የመኖራችን ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ሲሉም ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment