(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 28/2010) በቅርቡ የተፈቱት ንግስት ይርጋና አግባው ሰጠኝ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በመከላከያ ታፍሰው ከታሰሩ በኋላ መለቀቃቸው ተነገረ።
እነ ንግስት ይርጋ ታስረው የተለቀቁት በቅርቡ ከወህኒ የተፈታውን አጋየ አድማሱን ለመቀበል ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ ይዘው ጎንደር አየር ማረፊያ በተገኙበት ጊዜ ነው።
አብረው የታሰሩት ዮሴፍ ወንዴ፣ ቶማስ ዘለቀና አንድ ሌላ ሾፌር እስካሁን አለመለቀቃቸው ታውቋል።
ዛሬ በመከላከያ ታፍሰው በአዘዞ ካምፕ ከታሰሩ በኋላ የተለቀቁት ንግስት ይርጋ ፣አግባው ሰጠኝ፣አጋየ አድማሱ፣አንጋው ተገኝ፣ዘለቀ አስማረው፣አባይ ዘውዱ፣ ተገኝ ሲሳይ፣ ሰጠኝ ቢልልኝ፣ እስክንድ ኪኮ እና ሌሎችም ናቸው።
የጎቤ ምክትል የነበረው አጋየ አድማሱ ከእስር ተፈቶ ወደ ጎንደር ሲመለስ በአየር ማረፊያው በርካታ ሰዎች እርሱን ለመቀበል ታድመው ነበር።
በዚሁ የአቀባበል ስነስርአትም ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ በመያዛቸው ሕገመንግስቱን ጥሳችኋል በሚል የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሁሉንም አፍሰው አዘዞ ካምፕ ካሰሯቸው በኋላ እንደለቀቋቸው ለማወቅ ተችሏል።
አብረዋቸው የታሰሩት ዮሴፍ ወንዴ፣ ቶማስ ዘለቀና አንድ ሌላ ሾፌር እስካሁን አለመለቀቃቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
መከላከያ ሀገር ጠባቂና ድንበር አስከባሪ ነው ቢባልም የከተማዋ ፖሊስ በመሆን የማሰርና የመግረፍ ስልጣን ይዞ ከሕግ ወጭ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይታወቃል።
በተለይም በአሁኑ ጊዜ ሀገር እየተረጋጋና ለውጥ እየመጣ ነው እየተባለ ባለበት ወቅት በሕወሀት የሚመሩ የመከ፡ላከያ ሀይሎች ብጥብጥ ለማሰነሳት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ተነግሯል።
ንግስት ይርጋም ሆነ አግባው ሰጠኝ እንዲሁም ሌሎች አብረዋቸው የታሰሩ ሰዎች በጎንደሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ የሰላማዊ ትግል ምልክቶችና አራማጆች ነበሩ።
በወቅቱ ሕዝባዊ ትግሉ በመባባሱም ወደ ማእከላዊ ተወስደው በርካታ ሰቆቃዎች ከተፈጸመባቸው በኋላ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በከፈሉት ዋጋ በቅርቡ ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።
የተፈቱት እነዚህ የሰላም ታጋዮች ግን ዛሬ ደግሞ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ ያዛችኋል ተብለው በጎንደር መከላከያ ካምፕ ከታሰሩ በኋላ መለቀቃቸው ታውቋል።
No comments:
Post a Comment