ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርላማ አባል መሆን እንደ አሁን ሰቆቃ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። የፓርላማ አባላት ድምጽ ሲሰጡ ”የመረጣቸውን ሕዝብ“ እና ህሊናቸውን አዳምጠው ሳይሆን “ጠርናፊያቸው” ባዘዘው መሠረት መሆኑ መቸም ቢሆን ምቾች የሚሰጥ ነገር ባይሆንም ነገ እንደምናየው አሸማቃቂ ጉዳይ አልነበረም። “በጠርናፊ ትዕዛዝ” ድምጽ መስጠት ነገ በዚህ ሰዓት በብዙዎች ህሊና ውስጥ የሚያደርሰውን መሸማቀቅ ያህል ያደርስ ነበር ብዬ አላስብም።
የነገው መሸማቀቅ ከእስከ ዛሬው ሁሉ ይለያል። ነገ ህግ ሆኖ እንዲያልፍ የይሁንታ ድምጽ የሚሰጡለት አዋጅ ሳሞራ የኑስንና ጌታቸው አሰፋን ከፓርላማው በላይ የሚያደርግ፤ የሳሞራና ጌታቸው ሎሌዎች በዜጎች ላይ ለሚያደርሱት ፍጅት ሽፋንና ከለላ የሚሰጥ ህግ መሆኑን ህሊናቸው ስለሚረዳ ድምጽ ሰጥተው ከአዳራሹ ሲወጡ የሚደርስባቸው ውስጣዊ መሸማቀቅ ይታየኛል። የፓርላማው አባላት ነገ የሚያፀድቁት ህግ አንድ ፋሽስታዊ ቡድን መላውን የመንግሥት መዋቅር እንዲቆጣጠር በድምጽ ብልጫ በይፋ የወሰኑበት ቀን ሆኖ ይመዘገባል። ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በመዋሉ ምክንያት ዜጎች እየተገደሉ ነው፤ ድጋፋቸውን ሰጥተው ካፀደቁበት ደቂቃ ጀምሮ በርካታ ዜጎች ይገደላሉ፣ ይገረፋሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ። ችግሮች ሳይፈቱ ግልጽ ሁከቶችን ብቻ በማስወገድ ወይን በማፈን የሚገኝ አሉታዊ ሰላም ዘላቂ እንዳልሆነ እንዲያው እጅግ አደገኛ መዘዝ እንዳለው ልቦናዎቻቸው ይነግሯቸዋል።
ለዚህ አዋጅ የድጋፍ ድምጽ መስጠት ከራስ አልፎ ለልጅ ልጆች የሚተርፍ ፀፀት ነው። ከዚህ ፀፀት መዳን የሚቻለው የሚያስከፍለው ዋጋ በጀግንነት ተቀብሎ ”አይሆንም“ የሚል ድምጽ መስጠት ነው። በነገው ዕለት የሚሰጥ የአንድ ሰው እንኳን “አይሆንም” ድምጽ ከፍተኛ ዋጋ አለው፤ ያ ሰው ከገዳዮቻችን አንዱ አይደለም።
No comments:
Post a Comment