Tuesday, March 6, 2018

ሃገሪቱን በጦር ማስተዳደር አይቻልም ተባለ

Image may contain: 1 person, sitting and outdoor(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2010) ሃገሪቱን በጦር ማስተዳደር ለመንግስቱ ሃይለማርያምም አልበጀም ሲሉ የአባገዳዎች ምክር ቤት ሊቀመንበር አባገዳ በየነ ሰንበቶ አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህና ለሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ለሃይማኖት አባቶችና ለአባገዳዎች የሚታዘዝ በመሆኑ ኮማንድ ፖስቱ አያስፈልገውም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት ሊቀመንበር አባገዳ በየነ ሰንበቶ የወቅቱን ሁኔታ በተመለከተ በሀገር ቤት ከሚታተም ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ይሄ ኮማንድ ፖስት የሚባለውን ነገር አልወደውም”ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የእሬቻ በአል በሰላም የተጠናቀቀው በኮማንድ ፖስቱ አይደለም ያሉት አባገዳ በየነ ሰንበቶ እኛ ሃገሪቱን ማረጋጋት አያቅተንም ሲሉም እድሉ እንዲሰጣቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
“በጦር ሃይል ማስተዳደር ለመንግስቱ ሃይለማርያምም አልበጀም”ያሉት የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አባገዳ በየነ ሰንበቶ በመጨረሻም የደርግ ወታደሮች ተመልሰው ወደ ሕዝብ የተቀላቀሉበትን ሁኔታም አስታውሰዋል።
“በእውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህ ነው፣በቀላሉ ይመለሳል፣ኮማንድ ፖስት አያስፈልገውም” በማለትም የማረጋጋቱን ተግባር ለሃይማኖት አባቶች፣ለአባገዳዎችና ለሃገር ሽማግሌዎች እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
ሕዝቡ የሽምግሌዎች፣የአባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ቃል ጠባቂ ነው”ማለታቸውም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በብጹእ አቡነ ማትያስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ትላንት አዲስ አበባ ላይ ባወጣው መግለጫ በመላ ሃገሪቱ ምህላ እንዲደረግ ወስኗል።

No comments:

Post a Comment