(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2010) በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገና ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የሃገሪቱ ሰላምና አንድነት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ገለጸ።
ኦፌኮ በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገበት ሁኔታና የጸደቀበት መንገድ ሕገወጥ በመሆኑ አንቀበለውም ብሏል።
አዋጁ ሕገመንግስቱን በጣሰ መልኩ የተፈጸመ በመሆኑም ጉዳዩን ለሚመለከተው የሕግ አካል ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ኦፌኮ ገልጿል።
የኦፌኮ መግለጫ እንደሚያመለክተው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የሃገሪቱ ሰላምና አንድነት በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ምክንያቱ ደግሞ አዋጁ የተደነገገበት ሁኔታና በፓርላማ የጸደቀበት መንገድ ሕገ መንግስቱን በጣሰ መልኩ መሆኑ ነው ብለዋል።
እናም ኦፌኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደማይቀበለው ነው የገለጸው።
እንደ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/መግለጫ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ለተከሰቱትና እየተከሰቱ ላሉት የሕግ ጥሰቶችና የዜጎች ጉዳት አሁን በአገዛዝ ላይ ያለው የሕወሃት/ኢሕአዴግ አስተዳደር ሃላፊነቱን ይወስዳል።
ኦፌኮ ሕዝቡ ለዚህ አዋጅ እንዳይገዛም ይፋዊ ጥሪ አድርጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕግን በጣሰ መንገድ የተደነገገ በመሆኑም ጉዳዩን ለሚመለከተው ሕጋዊ አካል ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ኦፌኮ ገልጿል።
ኦፌኮ እንደሚለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕገመንግስቱ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ካለመውጣቱ ሌላ በፓርላማም 2/3ኛ ድምጽ ሳያገኝ ውድቅ የተደረገ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
በፓርላማ ጸድቋል የተባለውም ቁጥሩን በማጭበርበር ነው ሲል ኦፌኮ ሕጉን ጠቅሶ እንደማይቀበለው ገልጿል።
ኦፌኮ በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና አለምአቀፉ ማህበረሰብ ሃገሪቱ ያለችበትን ውስብስብ ችግር በመገንዘብ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።
No comments:
Post a Comment