(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 3/2018) በአማራ ሕዝብ ስም የተደራጁ 18 የፖለቲካና የሲቪክ ተቋማት በጋራ ተደጋግፎ ለመስራትና በተቀናጀ መልኩ ለመታገል መስማማታቸውን ገለጹ። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግም የአማራ ድርጅቶች አመራር ሰጭ አካል እንዲቋቋም በሜሪላንድ ሲሊቨር ስፕሪንግ ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 2 /2010 ባካሄዱት ዝግ ስብሰባ መወሰናቸውን ለኢሳት በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል። በመግለጫው እንደተመለከተው የአማራ ሕዝብ ለሃገሩ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውለታ የከፈለ ቢሆንም በጨቋኝነት ተፈርጆ ከፍተኛ በደልና ግፍ እየደረሰበት ይገኛል። በዚሁም ምክንያት እየደረሰበት ያለውን የመፈናቀል፣የማንነትና የህልውና አደጋዎችን ለመከላከል ድርጅቶቹ በተለያየ መልኩ ተደራጅተው ሲታገሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። እናም የምንታገልለት ሕዝብም ሆነ አላማ አንድ በመሆኑ የእስካሁኑን ትግል ውጤታማ ለማድረግ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል።
No comments:
Post a Comment