(ኢሳት ዜና
ከሚኖሩበት ሰሜን አሜሪካ ወደ አገራቸው በመግባት ከአገዛዙ ባለስልጣናት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሳይኖራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መዋእለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በግሉ የንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ በጣት ከሚቆጠሩ ባለሃብቶች አንዱ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ድርጅታቸው ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ኪሳራ ላይ እንዲገባ መደረጉን ከሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
አቶ ኤርሚያስ የአክሰስ ሪል ስቴት የጥበቃ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ባለቤት የሆኑት ኮሎኔል አብርሃ ስላደረሱባቸው የመብት ጥሰቶች ሲገልጹ” በወር የ540 ሰራተኞች 750 ሺህ ብር በወር ከፍለናል። በተግባር ግን ከ120 ሰው በላይ ተሰልፎ አያውቅም። በወር ወደ 500 ሽህ ብር የተጭበረበረ ነበር። ፖሊስ ጣቢያ ከስሻለሁ። ይህን አልፈርምም ስል በጣቱ እያሳየኝ ኤርሚያስ እኔ እኮ አሁን ግንባርህን ብልህ እኔ ባለኝ ኮኔክሽን ከእስር እንደምወጣ አታውቅም ወይ? ሲል አስጠነቀቀኝ። ፖለቲከኞችንና የሚሊቴሪ ስሞችን እየጠራ የማይደፈሩ ስሞችን ሳሞራ፣ ስብሃት እያለ እየጠራ አስፈራራኝ። የቤተመንግስቱን ጥበቃ ያደራጀሁት እኔ ነኝ፣ የኤርትራን ጦርነት መሃል ግንባር የመራሁት እኔ ነኝ
ብሎ ደንፍቶብኛል። ይህን ሳቀርብ ነው ከቦርድ ያወረዱኝ። ዓይኔን ጨፍኜ 22 ሚሊዮን ብር ብከፍል ኖሮ” እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ አልገባም ነበር፣ ቃና ላይ የተሰራው ድራማ ነው የተሰራብኝ። ድርጅቱ ተጠልፏል ምርመራ ይፈልገዋል።” ብለዋል።
ሌላው የአገዛዙ የቅርብ ሰው የሆነው የማስታወቂያ ሰራተኛው አቶ ሳምሶን ማሞ፣ “ገንዘብ ካልተከፈለኝ በጋዜጣዬ ስምክን አጠፋዋለሁ” በማለት ዝተው በመጨረሻም የድርጅታቸውን ስም የሚያጠለሽ ሪፖርት እንዳወጣ ተናግረዋል። ባለሃብቱ ሁኔታው ሲገልጹ ”ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ መርከብ ገዝቷል፣ ዱባይ ሆቴል ገዝቷል፣ 1.4 ቢሊዮን ብር ይዞ ተሰወረው የሚሉ ለመናገር የሚያስጸይፉ ዘገባዎችን በፊት ገጹ ላይ የእኔን ሙሉ ምስል በትልቁ ይዞ ወጣ። ሰኞ እለት ይህን የጋዜጣውን ዘገባ ያነበቡ ቁጥራቸው 400 የሚሆኑ የቤት ገዢዎች በክስተቱ ተደናግጠው መጥተው ቢሮውን አፈራረሱት። በስፍራው ሁከት ተፈጠረ፣ ከዛን በኋላ ማን ይመልሰው? የአክሰስ ሪል ስቴት ጉዳይ ወደ ሁከት እንዲገባ የተደረገው ሆን ተብሎ በጋዜጣው ባለቤት አቶ ሳምሶን ማሞ ነው።” ብለዋል።
ለ128 ቀናት ታስረው መውጣቸውንና ጉዳዩ በሕግ መያዙን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ፣ ከክስተቱ በኋላ የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ አዘጋጅ ”አንድ ሚሊዮን ብር እፈልጋለሁ ይህን ካልሰጣችሁኝ ጋዜጣ ላይ አወጣዋለሁ” ማለቱን፣ ያንኑ ሳምንት ምክትላቸው አቶ ሄኖክን ከመኪና ሲወርድ ሽጉጥ የያዘ ሰው እንዳፋጠጠው፣ አራት ደኅንነቶች ይዘው 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደመረመሩት” አጋልጠዋል። አቶ ኤርሚያስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የማእድን ውሃ ፋብሪካን ያስተዋወቁ ነበሩ።
No comments:
Post a Comment