(ኢሳት ዜና ማጋቢት 04 ቀን 2010 ዓ/ም) የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን መስፋፋትና የመሬት ቅርምት በመቃወማቸው ብቻ ከሚማሩበት ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከታሰሩ ተማሪዎች ውስጥ የተወሰኑት ቢፈቱም ቀሪዎቹ አስታዋሽ አጥተው ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ። በዲላ ዩኒቨርሲቲ ኢንጅነሪንግ ፋኩልቲ ተማሪ የሆኑት ወየቻ ታምሩ፣ ወሰኑ ገረመው፣ ዮሃንስ ፉርጋሳ፣ ገዳ ገመቹ፣ ኢዮብ ሙሊሳ እና ሳሎ ነጋሳ በእስር ቤት በሚፈጸምባቸው ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችን ጨምሮ ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው እርቀው በመታሰራቸው ጠያቂና አስታዋሽ አላገኙም። ተማሪዎቹ በችግር ላይ እንገኛለን ሚዲያም ሆነ ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች እያስታወሱን አይደለም ብለዋል። ተማሪዎቹ እጃቸው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት በመቀያየር እንዲገላቱ ተደርገዋል። ወንጀል ፈጽመዋል ወደተባለበት አካባቢ ሄደው እንዲዳኙ ተብሎ ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ወደ ዲላ ከተማ ቢዛወሩም ሀምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ወደ ሃዋሳ እንዲዛወሩ ተደርጎ አሁንም ካለ ፍትሕ በእስር ላይ ይገኛሉ። ከመሃከላቸው በተመሳሳይ ክስ ተከሶ የነበረው ቦረና አበራ የካቲት 7ቀን 2010 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ በነፃ ሲሰናበት ቀሪዎቹ እንዲከላከሉ ቢበይንባቸውም አንከላከልም በሚለው አቋማቸው መጽናታቸውን ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
No comments:
Post a Comment