Tuesday, March 27, 2018

የስዩም ተሾመ ጉዳይ በልዩ ሁኔታ በሚቋቋም ፍርድ ቤት ይታያል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2010)የመምህሩና ጦማሪው ስዩም ተሾመ ጉዳይ በልዩ ሁኔታ በሚቋቋም ፍርድ ቤት እንደሚታይ ተገለጸ።
መደበኛው ፍርድ ቤትም በፖሊስ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት መዝገቡን ዘግቷል።
በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም በአዋጅ የተከለከለ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሷል በሚል ከአምቦ ዩኒቨርስቲ ወልቂጤ ካምፓስ የታሰረው ስዩም ተሾመ ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲታይ ነበር።

ይህም ሆኖ ግን የስዩም ተሾመ ጉዳይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ልዩ ፍርድቤት ተቋቁሞ እንደሚታይ ፖሊስ በመጠየቁ መዝገቡ ተዘግቷል።
ፖሊስ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት በደብዳቤ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የስዩም ተሾመ ጉዳይ በልዩ ፍርድ ቤት እንደሚታይ ለማወቅ ተችሏል።
ጦማሪ ስዩም ተሾመ ክስ ያልተመሰረተበት ዋስትናም ያልተሰጠው ቢሆንም ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ለምን እንዳልቀረበ ፖሊስ ሲጠየቅ ጉዳዩ በልዩ ፍርድ ቤት ስለሚታይ ነው ብሏል።
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም አራዳ ምድብ አንደኛ ችሎትም ጥያቄውን ተቀብሎ መዝገቡን ዘግቷል።
ስዩም ተሾመ የካቲት 28/2010 ታስሮ የካቲት 30/2010 ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ በሁለት ተከታታይ ቀጠሮዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርብ መቅረቱ ታውቋል።
የጦማሪ ስዩም ተሾመ ጉዳይ በኮማንድ ፖስቱ በሚቋቋም ልዩ ፍርድ ቤት ይታያል መባሉ ሕግን የጠበቀ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ሕገመንግስት መሰረት ልዩ ፍርድቤት ማቋቋም ክልክል መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment