Monday, March 19, 2018

በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተጠራው የማስተጓጎል ዘመቻ በመጨረሻ ቀኑ ዛሬም በመካሄድ ላይ ነው።

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 10/2010) በሰሜን ጎንደር ሸሃዲ አካባቢ በአንድ የነዳጅ ማመላለሺያ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። በአንድ ሳምንት ግዜ ወስጥ የተቃጠሉ የነዳጅ ቦቴዎች ቁጥር ሶስት ደርሷል። በአዲስ አበባ የነዳጅ አቅርቦት ባለመኖሩ ጥቂት የማይባሉ ማደያዎች ዝግ ሆነው መዋላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በጎንደር ነዳጅ ለማግኘት ታክሲዎች ረጅም ሰልፍ ይዘው መቆየታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በባህርዳር፣ ደብረታቦርና ሌሎች ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ ዕጥረት መከሰቱም ታውቋል። ፎርቹን የተሰኘው አዲስ አበባ የሚታተመው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ አዲስ አበባ ሰሞኑን የገጠማትን የነዳጅ ቀውስ በተመለከተ ላሰፈረው ጽሁፍ የተጠቀመው ርዕስ ‘’አዲስ አበባን ነዳጅ ጠማት’’ የሚል ነው። ምንም እንኳን የአገዛዙ ባለስልጣናት ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንዳልተፈጠረ ቢገልጹም በመላ ሀገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት ላይ መስተጓጎል መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ናቸው። የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች በወታደራዊ አጀብ
እንደሚንቀሳቀሱ የአገዛዙ ደጋፊ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣም ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ ላይ አስፍሯል። ለአንድ ሳምንት የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን አስተባባሪዎቹ የሆኑት ቄሮዎች በተከታታይ ዘመቻ አገዛዙን የሚያዳክሙ አድማዎችን እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል። በዛሬው የመጨረሻ ቀን ዘመቻ እንደባለፉት ቀናት የነዳጅ ማደያ ቦታዎች ጭር ብለው ውለዋል። ሰሞኑን የነበራቸውን ክምችት እያወጡ ሲሸጡ የነበሩት አንዳንድ ማደያዎች የያዙትን በመጨረሳቸው ከትላንት ጀምሮ ቤንዚን የለም የሚል ማስታወቂያ በመለጠፍ ደምበኞቻቸውን ሲመልሱ እንደነበረ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ኢሳት ያነጋገራቸው የባህርዳር ነዋሪ ዛሬ የሚንቀሳቀስ የነዳጅ ተሽከርካሪ አለማየታቸውን በሁለቱም መስመሮች የሚንቀሳቀሱ እንዳልነበሩ ገልጸዋል። በክምችት የነበረው ነዳጅን በበርሜል ለተወሰኑ ደንበኞቻቸው ሲያከፋፍሉ የነበሩ ማደያዎችም የያዙት በማለቁ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ከባህርዳር ውጭ ባሉ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የነዳጅ አቅርቦት እንደሌለ ተገልጿል። መርሃዊና ዱርቤቴ መስመር የነዳጅ አቅርቦቱ ከተቋረጠባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በጎንደር ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች በተለይም የባጃጅ ታክሲዎች ነዳጅ ለማግኘት ተሰልፈው የሚታዩ ሲሆን አገልግሎቱ ባለመኖሩ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ከአካባቢው የኢሳት ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በደብረታቦርና ወረታም በተመሳሳይ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ትላንት ሰሜን ጎንደር ሸህዲ በሚባል አካባቢ አንድ የነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ተሽከርካሪ ላይ ርምጃ መወሰዱን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። ዘመቻው ከተጀመረ ለሶስተኛ ጊዜ በሆነው በዚሁ ጥቃት ተሽከርካሪው ላይ የቃጠሎ አደጋ እንዲደርስበት መደረጉ ታውቋል። ባለፈው ሳምንት ውስጥ በሰሜን ጎንደር ጭልጋ እና በምስራቅ ጎጃም አማኑዔል በተባሉ አካባቢዎች የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ከነጫኑት ነዳጅ መቃጠላቸው የሚታወስ ነው።

No comments:

Post a Comment