(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2010) አርበኞች ግንቦት ሰባት አንድ የሕወሐት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር መግደሉን አስታወቀ። ፋይል የተገደለው ከፍተኛ የሕወሃት ወታደራዊ አመራሩ የኮለኔልነት ማእረግ ያለው መሆኑ ተገልጿል። ኮለኔሉ ከመከላከያ ማዕከላዊ እዝ ሐይል የተወሰኑ ወታደሮችን በመያዝ ለከፍተኛ ተልእኮ ከሽሬ ወደ ጎንደር በማምራት ላይ እያለ የግንቦት ሰባት ታጣቂዎች ትናንት ረቡዕ ሊማሊሞ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት መገደሉን የግንባሩ ሕዝብ ግኑኝነት አስታወቋል። የአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝብ ግኑኝነት እንዳስታወቀው ኮሎኔል ሐብቶም የተባለው የሕወሀት ወታደራዊ ኣዛዥ በአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች የተገደለው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ከተማ አለፍ ብሎ ሊማሊሞ አካበቢ ነው። ረቡዕ መጋቢት 5/2010 ከምሽቱ 2 ሰአት አካባቢ የተገደለው ኮለኔል ሃብቶም የመከላከያ ማዕከላዊ እዝ የሀይል አመራር አባላትን ይዞ ወደ ጎንደር ለወታደራዊ ተልኮ ሲንቀሳቀስ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል። ኮለኔሉ በአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ጥቃት ደርሶበት ሲገደል አንድ አጃቢውም በከፍተኛ ደረጃ የመቁሰል አደጋ እንደ ደረሰበት የንቅናቄው የህዝብ ግንኙነት መግለጹን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በአካባቢው የተፈጠረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎም ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጣቂዎች ተልእኳቸውን ፈጽመው መሰወራቸውን በመግለጫው ተመልክቷል። የኮሎኔሉ አስከሬን ዛሬ መጋቢት 6/2010 ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ ወደ ትግራይ መላኩንም ንቅናቄው አስታውቋል።
No comments:
Post a Comment