(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 28/2010) በኦሮሚያ ከተነሳው አድማ ጋር በተያያዘ አምስት የኦሕዴድ የዞን ባለስልጣናት መታሰራቸው ተነገረ።
በኦሮሚያ የተጀመረው አድማ ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ውሏል።
ባለስልጣናቱ የታሰሩት የስራ ማቆም አድማው እንዲካሄድ ቅስቀሳ አድርገዋል በሚል ነው።
በኦሮሚያ ክልል በአገዛዙ የኮማንድ ፖስት አባላት የታሰሩት የኦሕዴድ የዞን ባለስልጣናት የምስራቅ ሃረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪን የሚጨመር ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አድማ ቀስቅሳችኋል ተብለው ከታሰሩት መካከልም የነቀምቴ ከተማ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ፣የምዕራብ ወለጋ ዞን ቄለም ወረዳ የፍትህ አስተዳደር ሃላፊም ይገኙበታል ተብሏል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኦሕዴድ ባለስልጣናት መካከልም ያለመከሰስ መብት ያላቸው የክልል ምክር ቤት አባላት እንደሚገኙበትም ነው የተገለጸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው አድማ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉ ታውቋል።
ከየካቲት 26/2010 ጀምሮ በተጠራው የሶስት ቀናት አድማ የንግድ እንቅስቃሴዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።
በዚሁ አድማ መንግስታዊ ተቋማትና ባንኮች እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተቋማትም ተዘግተው መዋላቸው ነው የተነገረው።
ለ3ኛ ቀን በቀጠለው አድማም በአዲስ አበባ አሸዋ ሜዳ በከተማዋ ዙሪያ ያሉት ሰበታ፣ለገጣፎ፣ፉሪና ቡራዩ እንዲሁም መላው አካባቢም ከእንቅስቃሴ ተገቶ ውሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ጅማ፣አጋሮ፣መቱ፣ወለጋ፣ነቀምቴ፣ነጆ፣ቄለም ወለጋና ደምቢዶሎ የአድማው ተሳታፊዎች ሆነዋል።
የአምቦ ከተማም በከፍተኛ የአመጽ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።
ሪፖርተር እንደዘገበው ደግሞ አምቦ ለሁለት ለሊቶች በተኩስ ስትናወጥ ነበር።
በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው አድማ ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ሁኔታው አስፈሪ መሆኑን በመግለጽ በአካባቢዎቹ የምግብና የጤና አገልግሎት ሊቋረጥ እንደሚችል በማስጠንቀቅ ከአዲስ አበባ ውጪ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ መክሯል።
ኤምባሲው እንደሚለው በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ ድንገት አመጽ ሊቀሰቀስና ሊፈነዳ ይችላል።
No comments:
Post a Comment