Tuesday, March 13, 2018

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ለተፈጠረው ቀውስ ዋናው መንስኤ የስልጣን አተያይ እና የድርጅት የመበስበስ ችግር መሆኑን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገለጹ።

 ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወጥቶ ከብሄር ድርጅትነት ወደ ሃገራዊ ፓርቲነት ለመቀየር በቀጣዩ ጉባኤ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚቀርብም ገልጸዋል። የኢሕአዴግ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንዳሉት ግንባሩ ወደ ውህድ ፓርቲነት ከመቀየሩ ሌላ የአጋር ድርጅቶችም ጉዳይ የዚሁ አካል እንዲሆኑ ታሳቢ እየተደረገ ነው። ኢሕአዴግ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲነት ለመሸጋገር ጥናት ያስፈልጋል በሚል ትቶት የቆየውን ጉዳይ ያነሳው የሕዝቡን ተቃውሞ ለመሸንገል መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት የሕዝቡ ተቃውሞ ተባብሶ ቀውስ ውስጥ ለመግባት የተቻለው ውስጣዊ የስልጣን ብልሽትና የድርጅት የመበስበስ ችግር ኢሕአዴግን ስላጋጠመው ነው። እናም ችግሩን ለማስወገድ ኢሕአዴግ አደረጃጀቱን መፈተሽ አለበት ብለዋል። እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ ኢሕአዴግ ከብሔራዊ አደረጃጀት ወጥቶ በዘላቂነት ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲነት መሸጋገር ይኖርበታል። ይህንኑ በተመለከተም የኢሕአዴግ ስራአስፈጻሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብ ተስማምቷል ነው ያሉት። በዚሁም መሰረት ኢሕአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ፓርቲ አደረጃጀት ለመቀየር በመጪው ነሐሴ በሚካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚቀርብ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ
ጠቁመዋል። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንደገለጹት ኢሕአዴግ ወደ ውሁድ ፓርቲነት ከመሸጋገሩ በተጨማሪ አጋር ድርጅቶችም የዚሁ አካል የሚሆኑበት ሁኔታ ይመቻቻል። ይህም በቀጣዩ የኢሕአዴግ ጉባኤ ይታያል ነው ያሉት።በሌላ በኩል የፓርላማ አባላት ካፓርቲያቸው ፖሊሲ ተጻረው ድምጽ መስጠት እንደማይችሉም አቶ ሽፈራው ገልጸዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነመናብርት ስምምነት ከደረሱና አባላቱም ለየብቻ እንዲወያዩበት ተደርጎ ከተቀበሉት በኋላ በፓርላማ የኦሕዴድ ተመራጮች መቃወማቸው ትክክል አይደለም ሲሉ ተችተዋል። የፓርላማ አባላት በአፈጻጸም ላይ መከራከር ይችላሉ እንጂ የተለየ አቋም ካላቸው ክርክሩን ማድረግ የሚችሉት በፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ ብቻ ነው ባይ ናቸው። ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ፓርቲነት እሸጋገራለሁ ማለቱን በተመለከተ የፖለቲካ ተንታኞች ሂደቱ የሕዝቡን ተቃውሞ ለመሸንገል የታለመ ነው ብለዋል።

No comments:

Post a Comment