አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ካቀረቡ ከአርባ ቀን በኋላ እና በመጀመሪያ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለብዙ ቀናት ቀጥሎም ምክር ቤቱ ከአንድ ሳምንት በላይ የፈጀ ስብሰባ ከተቀመጠ በኋላ ዶ/ር አቢይ አህመድን የግንባሩ ሊ/ቀመንበር አድርጎ መርጧል። የዶ/ር አቢይ የኢህአዴግ ሊ/መንበር ሆኖ መመረጥ የሚቀጥለዉ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ማን ሊሆን ይችላል በሚል በአትኩሮት ሲጠበቅ ለነበረው ጥያቄ የመጀመሪያ ዙር ምላሽ ሰጥቷል። ለመሆኑ የዶ/ር አብይ መመረጥ የተለመደው የወያኔ የሴራ አካሄድ ውጤት ነዉ? ወይስ ኢህአዴግ የህዝብን እውነተኛ የለውጥ ፍላጎት ሰምቶ መንገዱን ለማስተካከል የወሰደዉ ዕርምጃ ነዉ? የኢህአዴግ ዉሳኔ እነዚህን ጥያቄዎች ያጠቃለለ ጥልቅ ውይይት ተካሂዶበት የተወሰነ መሆኑንና ያለመሆኑን በቅርቡ የምንሰማውና በተግባርም የምናየው ይሆናል።
የዶ/ር አብይ መመረጥ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት እስካሁን የህወሀት ሎሌ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ድርጅቶችና በህወሓት ውስጥም ያሉ አንዳንድ ለውጥ ፈላጊዎች በጋራ አሸንፈው ከሆነና እነ ዶ/ር አብይ በተለይ በኦህዴድ ምክር ቤት ስብሰባ መግለጫ ላይ ያወጡትን ለውጥ ፈላጊ አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ ወስነው ከሆነ እሰየው ነው። የኢህአዴግ ዉሳኔ በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል፥ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ብሎም ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ለውጥ ፈላጊው ህዝብ ሁሉ የሚፈልገው ነውና በአዎንታዊ መልኩ የምንወስደው ነው።