ኢሳት (የካቲት 18 ፥2008)
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጀርባ የኤርትራ እጅ አለበት ሲሉ አዲስ ተቃውሞ ማቅረባቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አርብ ዘገበ።
መነሻውን ከጎረቤት ኤርትራ ያደረጉ አካላት በተቃውሞ ስለመሳተፋቸውንና ችግሩን በማባባስ ላይ ስለመሆናቸው በቂ ማስረጃ አለን ሲሉ የመንግስት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለዜና አውታሩ ገልጸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ላለው ተቃውሞ በክልሉ የመልካም አስተዳደር ተግባራዊ አለመደረጉ ነው ሲሉ ቢቆዩም ሃሙስ ከተቃውሞ ጀርባ የኤርትራ እጅ አለበት ሲሉ አስታውቀዋል።
ይኸው በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ተባብሶ የቀጠለው ተቃውሞ ሶስተኛ ወሩን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ድርጊቱም አለም-አቀፍ ትኩረትን ስቦ እንደሚገኝ የዜና ወኪሉ በዘገባው አመልክቷል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰው ይኸው ተቃውሞ አድማሱን በማስፋት የመደብና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን አካትቶ መቀጠሉን አለም አቀፍ ተቋማት በመግለፅ ላይ ሲሆኑ አሜሪካም ተቃውሞው ከማስተር ፕላኑ ያለፈ ጥያቄን ያነገበ እንደሆነ በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና፣ የመንግስት ባለስልጣናት የኤርትራ መንግስት ከተቃዋሚ ሃይሎች ተባብሮ በመስራት በሁከት በማተራመስ ላይ ነው ሲሉ አዲስ ቅሬታን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተባብሶ ለቀጠለው ተቃውሞ ኤርትራን ተጠያቂ ቢያደርግም ኤርትራ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠችው ምላሽ የለም።
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከተቃውሞው ጋር በተገናኘ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻሉ።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትም የፀጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የሃይሎች እርምጃ በማውገዝ መንግስት ለተቃውሞው ሰላማዊ ምላሽን እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ለሶስተኛ ወር በመካሄድ ላይ ባለው ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎችም በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት እነዚሁ አካላት ጥያቄን ማቅረባቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment