Monday, February 8, 2016

በኮንሶ የልዩ ሃይል ፓሊስ አባላት ጉዳት እያደረሱብን ነው ሲሉ ወጣቶች ተናገሩ

ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከኮንሶ የአስተዳደር ክልል ጋር በተያያዘ የተነሳውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር በአካባቢው የተሰማሩ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት ፣ መንገድ ላይ ያገኙዋቸውን ወጣቶች በመደብደብ አካላዊ ጉዳት እያደረሱባቸው መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ወጣቶች ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በፎቶ አስደግፈው በላኩት መረጃ፣ የፖሊስ አባላት በወጣቶች ላይ ድብደባ በመፈጸም፣ ማንኛውም የአካባቢው ወጣት ጥያቄ እንዳያነሳ ለማድረግ ይሞከራሉ ብለዋል።
በኮማንደር ፍስሃ ጋረደው የሚታዘዘው ልዩ ሃይል ጥር 26፣ 2008 ዓም ለሚ በርሻ የሚባል ወጣት ክፉኛ ተድብድቧል። ከእርሱ ጋር የነበሩ 14 ወጣቶም ተመሳሳይ ድርጊት ከተፈጸመባቸው በሁዋላ በአሁኑ ሰአት የት እንዳሉ... አይታወቅም።
የልዩ ሃይል አባላት ከሚፈጽሙት የሰብአዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ፣ ሜዳ ላይ ያገኙዋቸውን ፍየሎችና በጎች እየዘረፉ እንደሚበሉ ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።


ለጠ/ ሚኒስትሩ በድጋሚ አቤቱታ ለማቅረብ አ/አ የሚገኙት የሀገር ሽማግሌዎችና የኮንሶ ህዝብ የመረጣቸው ኮምቴዎች አደረጃጀታቸው ከወረዳ ወደዞን እንዲያድግ በሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸው ብቻ እስር፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት፣ ከስራ መፈናቀልና የመሳሰሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙባቸው ነው።
ሽማግሌዎች የክልሉ ሹማምንት ህዝቡን በማበሳጨት የሀይል ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ ለቀጣይ እርምጃቸው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው ካሉ በላ ይህን ህገወጥ ድርጊት እንዲያስቆሙ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ ለጠ/ ሚኒስትሩ በድጋሚ አቤቱታ እያቀረብን ነው ብለዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት የኮንሶ ህዝብ ተወካዮችን አነጋግረው ጉዳዩን አጣርተው በአጭር ጊዜ መልስ ለመስጠት ቃል ቢገቡም፣ በተቃራኒው በክልሉ ልዩ ሀይል የአፈና ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉ ጥያቄያችንን መመለስ እንደደተሳናቸው አስገንዝቦናል ሲሉ የአገር ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ለሚገኘው ዘጋቢያችን ገልጸዋል።
"የኮንሶ ህዝብ ሰላም ፈላጊ ነው" ያሉት ሽማግሌዎቹ፣ ሰላማዊ ጥያቄን በህገወጥ መንገድ ለመመለስ መሞከር ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል የደቡብ ሹማምንት ሊዘነጉት አይገባም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኮንሶ አካባቢ ከተፈጠረው ውጥረት ጋር ተያይዞ ት/ ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቁዋማትና ድርጅቶች ስራቸውን ማከናወን አልቻሉም።

No comments:

Post a Comment