Thursday, February 4, 2016

በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ላይ ፍርድቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ ተከሳሾቹ ችሎቱ እንዲቀየርላቸው ጠየቁ

ጥር ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ  እየተጉላሉ መሆናቸውን በመግለጽ ችሎት እንዲቀየርላቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አሰሙ።


 በዛሬው እለት ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረቡት ተከሳሾች አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ት እየሩሳሌም ተስፋው፣ አቶ ፍቅረማርያም አስማማው እና አቶ ደሴ ካህሳይ ጉዳያቸውን እያየ የሚገኘው ችሎት ጉዳያቸውን በማጓተት እያጉላላቸው መሆኑን በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡ መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ለብይን ቢሆንም ተከሳሾች 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታ በማሰማታቸው ብይኑ ሳይሰማ ቀርቷል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ‹‹አቃቤ ሕግ አንድ ምስክሩን ያሰማው ነሐሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ የአንድ ምስክር ቃል በጽሁፍ ተገልብጦና ተመርምሮ ብይን ለመስራት ይህን ያህል ጊዜ መውሰድ አልነበረበትም፡፡ ለዚህ ሁሉ መጉላላት ይህ ችሎት አስተዋጽኦ አለው ብለን ስለምናምን ችሎቱ እንዲቀየርልን ለፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ቢሮ አቤት ብለናል፡፡ ስለዚህ ብይኑ ዛሬ ሊሰማብን አይገባም›› ብሏል፡፡

3ኛ ተከሳሽ አቶ ፍቅረማርያም አስማማው በበኩላቸው ''ችሎቱ ለአቃቤ ህግ ወገንተኝነት ያሳያል ብለን ስለምናምን ችሎቱ እንዲቀየርልን የጠየቅነው አቤቱታ ላይ ብይን ሳይሰጥ ጉዳያችንን ችሎቱ እንዳያይ ይደረግልን'' ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

በተጨማሪም 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ደሴ ካህሳይ በበኩላቸው የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ መሆናቸው ታውቆ አስተርጓሚ እንዲመደብላቸው ቢጠይቁም እስካሁን ድረስ ግን አስተርጓሚ እንዳልተመደበላቸው ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment