Tuesday, February 23, 2016

በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ህወሃት/ኢህአዴግ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ለሶስተኛ ወር ቀጥሎ ያለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማክሰኞ አስታወቀ።
በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በክልሉ በበርካታ አካባቢዎች እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጀርባ የጥፋት ሃይሎች ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደራጁ የጥፋት ሃይሎች ያሏቸውን አካላት በስም ባይጠቅሱም መንግስትን የማፈራረስና የመቀየር ተልዕኮ አላቸው ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ድርጊቱንም ለመቆጣጠር መንግስት የማያዳግም እርምጃን እንደሚወስድ ገልጸው በምዕራብ አርሲና በሃረር አካባቢዎች ተቃውሞ መቀጠሉን አመልክተዋል።
የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን የሃይል እርምጃ በማውገዝ የኢትዮጵያ መንግስት ከድርጊቱ እንዲቆጠብና ለተቃውሞ ሰላማዊ ምላሽን እንዲሰጥ ማሳሰባቸው የታወሳል።
በክልሉ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ያለፉ የመብት ጥያቄን ያካተተ እንደሆነ የሚገልጹት እነዚሁ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ግድያን ማጣራት እንዲካሄድበት ጠይቀዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ሰኞ መግለጫን ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ሶስተኛ ወሩን በያዘው ተቃውሞ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክቷል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ያለው ተቃውሞ መፍትሄን እንዲያገኝ በመጠየቅ ላይ ቢሆኑም መንግስት የጥፋት ሃይሎች እጅ አለበት በማለት የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እንደሚቀጥል ማክሰኞ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment