Tuesday, February 16, 2016

ጥያቄህን ልመልስ-ልጄ | ከስርካለም ፋሲል

Serkalem Fasil Send A Voice Message To Her Husband (Eskinder Nega)
ለረጅም ግዜ ተራርቀን የማገኛቸው ጓደኞቼ ናፍቆትን ሲያዩት የሚጠይቁኝ “ያ ቃሊቲ የተወለደው ልጅ ነው በጣም አደገ” በማለት ነበር።
አንተም በተደጋጋሚ “ቃሊቲ” የምትለዋን ስም ስትሰማ፣ ቦታው ትምህርት ቤትም ሆነ መዝናኛ ስፍራ አለመሆኑን ጠንቅቀህ ስለምታውቅ፣ ጥያቄህ ፦
“ታስረሽ ነበር እንዴ ?…. እኔም ታስሬ ነበር?” የሚል ነው። ለብዙ ግዜ መልሱን በሽፍንፍን ነበር የማልፈው። ምክንያቴ ደግሞ፣ የመረዳት አቅምህን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር።
እስኪ ዛሬ ከ ዘጠኝ ዓመት በፊት ስለነበረው እውነተኛ ታሪክ ልተርክልህ። ምንም እንኳ አሁንም ትረዳኛለህ ባልልም።
ልጄ፣ “ታስሬ ነበር እንዴ እውነቱን ንገሪኝ?”…ለምትለኝ ፦
“አዎ። ለ9 ወራቶች ከማዕከላዊ -ቃሊቲ አብረን አሳልፈናል”
” ምን አድርጌ?… እጄ ላይ እንደእስክንድር ብረት ገብቶልኝ ነበር?” ….
ጥያቄህ ብዙ እንደሚሆን እገምታለሁ … እኔም ብዙ መልስ አለኝ። ለዛሬው ግን የታሰርኩበትን የመጀመሪያውን ቀንና የምጧን ሰዓት ብቻ ላውጋህማ።
ከ97 ምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ችግር…(ታሪኩ ሰፊ ነው) እኔና አባትህን ጨምሮ፣ በርካታ ሰዎች ለሞት፣ለስደት እንዲሁም ለእስር ተዳርገው ነበር።
ጥያቄህ አያልቅምና “የእኔ ሚና በምርጫው ውስጥ ምን ነበር?” ትለኝ ይሆን?…
መልሴ ምንም ነው ፍቅሬ። ምንም ውስጥ የለህበትም።
“ታዲያ እንዴት አሰሩኝ?”…አቤት ጥያቄህ…
በርካታ ሰዎች በምርጫው ሰበብ ታስረዋል ብዬህም አልነበር?..አንተ በቀጥታ ባትታሰርም፣ እኔ ስታሰር አንተን በሆዴ ይዤ ነበር። የአንድ ወር ተኩል ነብሰ ጡር ነበርኩ። ያልረጋ ፅንስ ይዤ ነው የመከራን ህይወት አንድ ብዬ መግፋት የጀመርኩት። እስክትወለድ ግዜ ያሳለፍኩት ግዜያቶች…. አቤት ስቃይህ። አቤት ስቃዬ። ከቃላት በላይ።
እኔና አባትህ የተያዝንባት የመጀመሪያ ቀን!
ህዳር 18/1998 ዓ.ም። ዕለተ-ዕሁድ። ኃይሌ ገ/ሥላሴ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው “ታላቁ ሩጫ” የሚካሄድበት ቀን። (ምናለ በዚህ ቀን ባልታሰርኩና ይሄ ቀን በመጣ ቁጥር ባላስታወስኩት)…ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ። የአጥር በራችን በኃይል ይንኳኳል።…. ግቢው ውስጥ የነበረች አንዲት ዘመዳችን
“ማነው?…እረ መጣሁ..ቀስ በሉ” እያለች የግቢውን አጥር ከፈተች።…. በሩን ስትከፍት ያጋጠማት ግን፣ጉንጯ ላይ ያልታሰበ ጥፊ ነበር። …(የአጥር ግቢውን መንኳኳት ተከትሎ እኔና አባትህ ሁኔታዎችን በመስኮት እየተከታተልን ነበር) …ቁጥራቸውን ልገምትልህ እችላለሁ። ወደ 10 የሚጠጉ የፌዴራል ፖሊስ፣ቁጥራቸውን ማስታወስ የማልችል ሲቪል ለብሰው መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች በመንጋ(እንደ ንብ ) ግቢው ውስጥ ዘለቁ።
ክላሻቸውን ወድረው ቤታችን ውስጥ ተሰገሰጉ። ልጄ፣ በአንድ ግዜ ቤቱን ጦር ሜዳ አስመሰሉት። ከዚያስ?..ከዚያማ … አቤት የሰው ልጅ ጭካኔ!….(አባትህ በተደጋጋሚ ልጄ ጥላቻ ይዞ እንዳያድግ ይላል። ቃሉን ተግብርለት እሺ!)….አባትህን በአንድ ክፍል፣እኔን በሌላ ክፍል ነጣጥለው አስቀመጡን።….በዱላ ብዛት እነሱ ወይስ እኛ ደከመን?…እኔንጃ። የማስታውሰው ነገር እኔ ክፍል ያለው ጠብደል የፌዴራል ፖሊስ ሲጫወትብኝ ብቻ ነው። እዚህ ላይ ልብ በልልኝ…”ሲጫወትብኝ” እንጂ “ሲያጫውተኝ” አለማለቴን። ….ይመታኛል…ይመታኛል….ህምምም!!…
“ምንሽን መታሽ?” አትበለኝ ልጄ። በዱላ የቀረው የሰውነቴ ክፍል ስለሌለ ” እዚህ ጋር፣እዚያ ጋር ” አልልህም።…በዚህ መካከል ሁሌም የሚገርመኝንና የማልረሳውን ግን ሳልነግርህ አላልፍም። ከመታሰሬ 2 ዓመት ቀደም ብሎ ከባድ የጤና ዕክል ገጥሞኝ ነበር። በዚያ ህመም ብዙ ተፈትኜበታለሁ። በወቅቱ እዚያ የጤና ዕክል ያጋጠመኝ የሰውነቴ ክፍል ላይ እንኳንስ ሲመቱኝ፣ሲያወሩኝ ስሜቴን ይረብሸው ነበር። እናማ…ይሄ ቅልብ ፌዴራል ያንን ቦታ እየደጋገመ በርግጫ ይለኝ ጀመር። ህመሜን ያወቀ ይመስል።-ህምምም!… ቢጨንቀኝና የዱላውን ቦታ ቢቀይርልኝ ብዬ
“እዚህ ጋር አትምታኝ ኦፕራሲዮን አለኝ” አልኩልሃ…..
ይህ ጨካኝ ፍጥረት ምን አለኝ መሰለህ?…
“ሙቺበት”…
ድምፁ ጆሮዬ ላይ አሁን ድረስ አለ”ሙቺበት”…ህምምም! (እንግዲህ ያልተቆረጠለት ነብስ አይወጣ እንዴት ልሙትበት?….) በመጨረሻም ከዱላው ጋብ አለና ባደረገው የወታደር ከስክስ ጫማ፣በአንደኛው እግሩ የተረከዙ ጫፍ የእግሬ ጣቶች ላይ ቆሞ ተሸከረከረብኝ። (ማለትም፣ ማንም ሰው በአንድ እግሩ የተረከዙ ጫፍ ላይ ቆሞ መሽከርከር)….ከዚያ ምን ሆነ መሰለህ ልጄ …እግሬ ላይ ያለው ቆዳ በከፊል ተገሸለጠ። ቆዳ ሲላጥ ደግሞ፣ ደም እያቸፈቸፈ ማቃጠል ብቻ….እስኪ የእኔ ይብቃህና ወደ አባትህ ልመልስህ፦
ከላይ እንደገለፅኩልህ አባትህን ሌላ ክፍል ወስደውታል ብዬህም አልነበር?…የእኔ ዱላ ጋብ ሲል የእሱን አዳምጥ ገባሁልህ። ….ጓ…ጓ..ጓ… የፈጣሪ ያለህ! የማያቋርጥ ጓጓታ። … የእኔ ዱላ ካቆመ ቢያንስ ከ 15 ደቂቃ በኅላ፣ እኔ ያለሁበት ክፍል ይዘውት መጡ።
ልጄ፦ ከሰዓታት በፊት አጠገቤ የነበረው እስክንድር አልመስልሽ አለኝ።
“እና ማነው?”…ብለህ ትጠይቀኝ ይሆን?….ህምምም!
…ወደ ክፍሌ የዘለቀውማ አባትህ ነው። ግን፣ግን… ፊቱ በደም ተነክሯል። በተለምዶ አንጎል ብለን የምንጠራው የጭንቅላታችን ክፍል ላይ በቀኝም በግራም በኩል ብይ የሚያካክሉ ዕባጮች ይታዩኛል። …. ክፉኛ ጎድተውታል። ከጥቂት ደቂቃ በፊት እኔ ላይ የደረሰውን ሁሉ ዘንግቼ፣ ያ “ጨካኝ” የፌዴራል ፖሊስ አጠገቤ መቆሙንም ረስቼ ” አፈር ልብላልህ ” ስል መናገር….አላስችል ብሎኝ እንጂ ምነው በቀረብኝ።…ከየት መጣ ሳልል ሲቪል የለበሰ ግለሰብ “ሸርሙጣ” ብሎ በጥፊ ያጣድፈኝ ጀመር…ህምምም!(አባት ሆይ ጥላቻንና ቂምን ከእኔ አስወግድልኝ)….
እስክንድር እኔ በነበርኩበት ክፍል ብዙም አልቆየ። ያመጡትም የእጅ ስልኩን (ሞባይሉን) እንዲሰጣቸው ነበር። የእኔንም አብረው ወሰዱት። ከዚያማ….እኔን ሲደበድበኝ ለነበረው የፌዴራል ፖሊስ “ጠብቃት”ብለው እስክንድርን ይዘውት ወጡ። ከቤት ብቻም ሳይሆን ከግቢ። ….በግምት ከ1 ሰዓት በኅላ እኔ ወዳለሁበት ክፍል አንድ ሲቪል የለበሰ ግለሰብ፣ለፖሊሱ “ይዘሃት ና” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈና በፍጥነት ወጣ።
“ተነሽ ቀጥይ”የፌዴራል ፖሊሱ ድምፅ።
እንዴት ልቁም… ሰውነቴ ዛል ብሏል። …. “ውሃ ጠጥቼ ልውጣ?” ስል ተማፀንኩት። አልከለከለኝም። በቁሜ አንድ ብርጭቆ ውሃ ጠጣሁናበእሱ አጃቢነት ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ።
ከአንድ ሰዓት በፊት ከእኔ የተለየው እስክንድር የፌዴራል ፖሊስ መኪና ውስጥ ቁጭ ብሎ አየሁት። የት አድርሰው መልሰውት ይሆን?…. እኔም እዚያ መኪና ውስጥ እንድገባ ተደረኩ። ምንም እንኳ ከሰዓታት በፊት አሰቃቂ ግፍ ቢፈፀምብንም፣ ሁለታችንም ስንተያይ ፈገግ አልን። ባዶ ፈገግታ። እክንድርና ኔና “አይዞሽ፣አይዞህ ” መባባል ስንጀምር ፣ምንም ዓይነት ንግግር ማድረግ እንደማይፈቀድልን አንዱ ሲቪል ለባሽ ቆጣ ብሎ ነገረን። ….ጉዞ ወደ ማዕከላዊ።
ማዕከላዊ እንደደረስን አንድ ቢሮ ደጃፍ ላይ ሁለታችንንም እንድንቀመጥ አድርገውን እኛን ያመጡን”ጀብደኞች” ጥለውን ሄዱ።
በዚህ መካከል ለአባትህ ሁለት ጥያቄ አቀረብኩለት
“አንጎልህ ላይ በምን መቱህ?”
“በሰደፍ”
“ከቤት ከወሰዱህ በኅላ የት ቆይታችሁ ነው ወደኔ በድጋሚ ያመጡህ?”
“ቦታውን አላውቀውም…በፍጥነት እየነዱ አደባባይ አሽከረከሩኝ”
(ካለፈ በኅላ “የእኛማ ሙሽራ”…ስል አንጎራጎኩ። እኔ አደባባይ ሲዞር የማውቀው ሙሽራ እንጅ እስረኛ ባለመሆኑ )
ልጄ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አንተን በሆዴ ይዣለሁ። ታሪክህ ይኸው ነው። ግን አልጨረስኩም። ይህንን ነገር ወደ ኅላ ተመልሼ ስተርክልህ ስሜት ውስጥ እንዳልገባና የነበረውን ዕውነታ ብቻ ነው በተቻለኝ መጠን የምገልፅልህ። አልጨረስኩም ዘንባባዬ እቀጥልልሃለው።

No comments:

Post a Comment