Monday, February 8, 2016

ከፍተኛ የፖሊስ እጥረት ተፈጠረ።

ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚካሄደውን ህዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ የፖሊስ እጥረት በማጋጠሙ፣ መንግስት ስልጠናቸውን ያላጠናቀቁትን ከማሰልጠኛ በማውጣት ከማሰማራት በተጨምሪ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የፖሊስ ልብስ እያለበሰ በማሰማራት ላይ ነው።
አብዛኛው የፌደራል ፖሊስ አባላት በኦሮምያ የተሰማሩ ሲሆን፣ በጋምቤላ እና በአማራ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የፖሊስ አባላትም ተሰማርተዋል። በክልሎች የሚታየው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ መንግስት የመከላከያ አባላትን በፖሊስ ዩኒፎርም እያሰማራ ከመገኘቱም በላይ ስልጠናቸውን ያልጨረሱ ፖሊሶች ሳይቀር ወደ ክልሎች እየዘመቱ ነው። በዚህም የተነሳ የመንግስት ተቋማትን የሚጠብቁ ፖሊሶች ቁጥር በማነሱ፣ ብዙዎቹ ፖሊሶች 24 ሰአታት ያለ እረፍት እንዲሰሩ ተደርጓል። አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል፣ "አሁን ያለንበት ሁኔታ በ97 ከነበረው ጋር ሲተያይ የከፋ እንጅ የተሻለ አይደለም" ብሏል። ፖሊሶች እረፍት የሚባል ነገር ሊያገኙ ባለመቻላቸው እንዲሁም ከህዝቡ ጋር መጋጨታቸውና በየጊዜው የሚደርስባቸው ውግዘት እየከበዳቸው ጥለው የሚጠፉ ፖሊሶች መብዛታቸው ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገውም ፖሊሱ ተናግሯል።

No comments:

Post a Comment