Monday, November 2, 2015

በባህርዳር የባጃጅ አሽከርካሪዎችን አድማ ለማስቆም መስተዳድሩ በሹፌሮች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው አርብ ጀምሮየስራ ማቆም አድማ ያደረጉት የባህርዳር የባጃጅ ሹፌሮች ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ የከተማው ሹማምንት እርምጃ እየወሰዱ ነው። ፖሊስ የቆመ ባጃጅ መኪኖችን ሲያገኝ ታርጋ ፈቶ ከመውሰድ ጀምሮ ሹፌሮችንም እያሰረ ይገኛል። የሹፌሮች አድማ መጠናከር በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እጥረት የፈጠረ ሲሆን፣ መስተዳድሩ ሌሎች መኪኖችን መድቦ አገልግሎት እንዲሰጡ አስገድዷል። ስራቸውን በማይጀምሩት ሾፌሮች ላይ መስተዳድሩ በማስፈራራቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ሹፌሮች ስራ ቢጀምሩም፣ በአብዛኛው አድማውን ዛሬም ቀጥለውበታል።

ሹፌሮች ተቃውሞውን ያደረጉት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት መምሪያ ተግባራዊ ያደረገውን የባጃጅ ስምሪት መመሪያ በመቃወም ነው። አሽከርካሪዎችና ባለሃብቶች አድማውን ከመጀመራቸው በፊት ሀሙስ ሌሊት የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ የጥሪ ወረቀት ሲለጥፉ አድረዋል፡፡ ባጃጆች በሚያድሩበት ቦታ ታርጋቸው እንዳይፈታ ባለሃብቶች እራሳቸው እንዲፈቱና በእጃቸው እንዲይዙ የጥሪው ወረቀት ያሳሰበ ሲሆን፤የገዢው መንግስት ወታደሮችና የከተማዋ ፖሊሶች የተለጠፉ ወረቀቶችን ሲገነጥሉ ማርፈዳቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
‹‹ ከአሁን በፊት በስራ ላይ የነበረው የስምሪት አገልግሎት አሰራር በአግባቡ ተግባራዊ አልተደረገልኝም፡፡ ›› ያለው የትራንስፖርት መምሪያው ሁሉም ባጃጆች ከጠዋት እስከ ማታ በተመደቡበት አቅጣጫ ብቻ እንዲሰሩ የደነገገ ሲሆን ይህን ለሚተላለፉ አሽከርካሪዎች የ400 ብር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስታውቋል፡፡መመሪያው አክሎ እንደገለጸው ማንኛውም ባጃጅ በኮንትራት፣በችግርም ሆነ በሌላ ምክንያት የስምሪት ቀጣናውን ለቆ ቢንቀሳቀስ ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሚሆንበት መደንገጉን ገልጿል፡፡ ለዚህም ከአሁን በፊት ባልታየ ሁኔታ የከተማዋን ፖሊሶችና የትራፊክ ፖሊሶችን በብዛት በማሰማራት ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከአሁን በፊት ተማሪዎችን ወደ ልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶች በኮንትራት የሚያመላልሱ ባጃጆች ከትምህርት ቤቱ ወይም ከወላጆች ጋር ውል በመያዝ ፈቃድ እንዲጠየቁ በመገደዳቸው ለጊዜው ስራቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከገበያ ፣ከመነኸርያና ከጊዮርጊስ – አባይ ማዶ የተመደቡት ባጃጆች ብዛት 350፤ከጊዮርጊስ – ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ድረስ የተመደቡት 65 እንዲሁም ከገበያ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ 300 ባጃጆች የተመደቡ መሆናቸውን የሚናገሩት አሽከርካሪዎች ፣ ከመብዛታቸው የተነሳ ምንም ስራ ሳይሰሩ ወረፋ በመጠበቅ ብቻ ቆመው ለመዋል ተገደዋል፡፡በአንጻሩ በዶናበር፣በገጠር መንገድና ሆስፒታል መስመር የተመደቡት ባጃጆች ቁጥር አንሶ ህብረተሰቡ በትራንስፖርት እጦት በየቦታው ተሰልፎ እንደሚውል የተናገሩት አሽከርካሪዎች የስምሪቱ አካሄድ ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየቦታው የተሰጠው ስምሪት በማህበራት በመሆኑና አንድ ማህበር እስከ 300 ባጃጅ ስላላቸው በአንዳንድ ቦታዎች ከሚፈለገው ቁጥር በላይ በመሆኑ ስራ ሳይሰሩ ለወጪ ከሚዳረጉ ቆመው መዋል እንደሚሻል ያሰቡ አሽከርካሪዎች በየቤታቸው ቆመው መሰንበታቸውን ተናግረዋል፡፡ከአስራ ሁለት ሰዓት በኋላ ህዝብ በሚበዛባቸው መስመሮች በመሰማራት፣ ለተለያዩ እንግዶች፣ ለህመምተኞች፣ መስመር በሌለባቸው አካባቢዎች ኮንትራቶችን በመስራትና ለተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የቀን ገቢያቸውን ለማግኘት ይሯሯጡ እንደነበር የሚናገሩት አሽከርካሪዎች፤ ዛሬ ‹‹ የትም እንዳትንቀሳቀሱ !! ›› በማለት የተደረገባቸው ማዕቀብ ለስራ ማቆም አድማ እንደገፋፋቸው ይገልጻሉ፡፡
በሌላ ዜና የብአዴንን 35ኛ በዓል ምክንያት በማድረግ የባህርዳር ከተማን መንገዶች በቀለም ለማሸብረቅ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ላይ መሆኑን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡በክልሉ ምስራቃዊ ክፍል ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ ህብረተሰቡ በችግር ላይ እያለ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጊዜያዊነት ተበጅቶ ያለአግባብ ወጪ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል ፡፡

No comments:

Post a Comment