ኀዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መምህር ወንድማገኝ አንጆሎ እና መምህር መስፍን በላይ የታሰሩት ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ማእከላዊ እስር ቤት ተወስደዋል። ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ምንቾች ገልጸዋል። መምህራሩ ከሰው ጋር እንዳይገናኙ ተደርጎ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
መምህር ወንድማገኝ ከመታሰራቸው በፊት ዩኒቨርስቲው የስራ እና የእግድ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። በመምህር ወንድማገኝ ላይ የቀረበውን ክስ መነሻ፣ የየኑቨርስቲ ባለስልጣናት የጻፉዋቸውን ደብዳቤዎች በመጨረሻም ግንቦት7 ተብለው ታፍነው ለምን እንደተወሰነባቸው ነገ በልዩ ዝግጅት አጭር ዘገባ እናቀርባለን።
በደቡብ ክልል ህገመንግስቱን በመናድ መንግስት ለመገልበጥ አሲራችሁዋል የተባሉ 12 የዩኒቨርስቲ መምህራንና የመንግስት ሰራተኞች በክልሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የ5 አመት እስራት ተፈርዶባቸው ከአመት በላይ በእስር ቤት ያሳለፉ ሲሆን ፣ ይግባኝ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅረባቸው ጉዳያቸው ጥቅምት 25 ይታያል። በእስር ላይ የሚገኙት መምህር አባተ ኢካ የሰመራ ዩኒቨርስቲ የሂሳብ አስተማሪ፣ መምህር ዱባለ ገበየሁ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የሶሳል አንትሮፖሎጂ መምህር፣ መምህር ጎሳሁን ዶሳ፣ የዳውሮ ዞን የማረቃ ወረዳ አቃቢ ህግ የሆኑት አቶ ግዛቸው ታደሰ፣ በዚሁ ወረዳ ሌለው አቃቢ ህግ የሆኑት ማለዳ ባተላ፣ በግልገል ጊቤ 3 ፕሮጀክት ሹፌር የሆነው ፍሬህይወት አባተ፣ አለሙ በቀለ፣ ተረፈ በቀለ፣ መስፍን መሸሻ፣ ተሰማ ደስታ፣ ጣሰው አበራ፣ አበራ ቡርቃና አርሶ አደር ታየ ታደሰ ናቸው።
በሌላ የፍርድ ቤት ዜና ደግሞ አይ ኤስ በኢትዮጵውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት ለመቃወም መንግስት በጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ሰበብ የታሰሩት ማቲያስ መኩሪያ፣ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ እና መሳይ ደጉሰው ህዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመናገሻ ምድብ ችሎት ቀርበው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
ችሎቱ በዝግ ቢሮ ውስጥ ከመታየቱም ባሻገር ችሎት አስከባሪው “መግባት አይቻልም ተከልክሏል ፣ የከለከልኩት ግን እኔ አይደለሁም!” በማለቱ ማንም እንዳይገባ ተከልክሎ በዝግ ታይቷል፡፡
ፖሊስ ተከሳሾቹ ላይ የቪዲዮ ማስረጃ አለኝ በማለቱ ተከሳሾቹም ‹‹የቪዲዮ ማስረጃው ለእኛም በመከላከያ ማስረጃነት ስለሚያገለግለን ይቅረብልን›› ባሉት መሰረት ቪዲዮውን አይቶ ብይን ለመስጠት ለወራት ሲቀጠርባቸው ቆይቷል፡፡
ከመሳይ ደጉሰው ውጭ ያሉት ተከሳሾች የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ፣ ተከሳሾቹ ከታሰሩ ከ6 ወር በላይ ካለፍርድ በእስር የተንገላቱ ሲሆን ይህንንም በተደጋጋሚ ጊዜ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም መልስ ማጣታቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። ፍርድ ቤቱ ለብይን ውሳኔ ለህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
No comments:
Post a Comment