ኢሳት ዜና :-ዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር የ2015 ዓ.ም የዓመቱ ኮከብ ሯጮች በማለት ኢትዮጵያዊቷ ትንሿ ልዕልት ገንዘቤ ዲባባ እና አሜሪካዊው አሽተን ኤተንን መርጧል።
የ24 ዓመቷ ወጣት የበቆጂ ፍሬ ገንዘቤ ዲባባ በዓመቱ ውስጥ በ1 ሽህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር በፈረንሳይ ሞናኮ እርቀቱን በ3 ደቂቃ 50.07 ሰከንድ ክብረወሰን ከመስበሯም በተጨማሪ በቻይና ቤጅንግ የአለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ በ1ሽህ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትና በ5 ሽህ ሜትር ርቀት ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ አይዘነጋም።የ27 ዓመቱ ወጣት አሜሪካዊው አሽተን ኤተን በበኩሉ የዓለም ዴክታትሎንና ሄፕታትሎን ክብረወሰን ባለቤት ነው።
ዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ለአትሌቶቹ በሞናኮ የሽልማት ስነስርዓት አላደረገም የዚህም ዋናው ምክንያት ማኅበሩ በሙስና ቅሌት በመዘፈቁ እንደሆነ ተገልጿል።
ዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ለአትሌቶቹ በሞናኮ የሽልማት ስነስርዓት አላደረገም የዚህም ዋናው ምክንያት ማኅበሩ በሙስና ቅሌት በመዘፈቁ እንደሆነ ተገልጿል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሰር ሰባስቲያን ኮ እንዳሉት ”እንደተለመደው የአትሌቲክስ ቤተሰቦች በአንድ ላይ በሞናኮ ታድመን የዓመቱን ኮከቦች በክብር ለመሸለም አልቻልንም።ገንዘቤና አሽተን በዓመቱ ውስጥ ላሳያችሁት ጽናትና ለእውነተኛ ስፖርት ምሳሌ በመሆናችሁ የምስራች ብያችኋለሁ! ”በማለት ሰባስቲያን ኮ ለኮከቦቹ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ከሽልማቱ በኋላ አስተያየቷን የተጠየቀችው ትንሿ ልእልት ገንዘቤ ዲባባ ስትመልስ ”ባለፈው ዓመት በጠባብ የነጥብ ልዩነት ይህን ሽልማት አጥቼዋለሁ አሁን ደግሞ በደጋፊዎቼ እና በስፖርት ጠበብቶች በመመረጤ ኩራት ተሰምቶኛል!”በማለት ደስታዋን ገልጻለች።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ሯጭ በመሆን በ1991ዓ.ም ለዚህ ሽልማት የበቃው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ሲሆን ከስድስት ዓመታት በኋላ እሱን ተከትሎ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በ1997 እና 1998 ዓ.ም አቦሸማኔው ቀነኒሳ በቀለ ሲሸለም በእንስቶች ደግሞ ብቸኛዋ ብርቅዬ ሯጭ መሰረት ደፋር በ2000 ዓ.ም የመጀመሪያዋ ቀዳሚ እንስት በመሆን ተመርጣለች።ትንሿ ልዕልት ገንዘቤ ዲባባም በበኩሏ ስሟን በታሪክ ማኅደር አስፍራለች።
No comments:
Post a Comment