ኀዳር ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለስድስት ከፍተኛ ጡረተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ለእያንዳንዳቸው በ25 ሚሊየን ብር ወጪ በስጦታ የሚለገሳቸው የመኖሪያ ቤት እየተገነባ መሆኑ ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ከሆነ በሁዋላ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡
በተለይ በረሃብ ምክንያት ከ 15 ሚሊየን ያላነሱ ወገኖችን ችግር ላይ በወደቁበት፣ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ ኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት በነገሰበት፣ የመንግስት ሠራተኛው ሳይተርፈው ሌት ተቀን ቦንድ ግዛ እየተባለ ከጉሮሮው እየተነጠቀ ደመወዙ በሚቆረጥበት ወቅት ለጥቂት ባለስልጣናት ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ቅንጦት የመኖሪያ ቤት እየተገነባ መሆኑ መሰማቱ ጉዳዩን የተከታተሉ ነዋሪዎችን አስደንገጧል።
አንድ ነዋሪ ለአዲስ አበባው ዘጋቢያችን በሰጠው አስተያየት መንግስት በዚህ ደረጃ ይዘቅጣል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፣ ይህን ዘግናኝ የሆነ ዜና መስማቴ እጅግ አሳዝኖኛል ብሎአል፡፡
አስተያየት ሰጪው በሙስናና ብልሹ አሰራር የሚታወቁ፣የሕዝብ ፍቅር የራቃቸውን የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለለስልጣናት ጡረታ ሲወጡ መሸለም ሕዝብን መናቅ ነው ካሉ በሃላ፣ ቢያድላቸው ኖሮ ትልቁ ሽልማት የሕዝብ ፍቅር በሆነ ነበር ፣
እነሱ ግን ለዚህ አልታደሉም ብሎአል፡፡ አንድ የህግ ባለሙያ ደግሞ በሕግም ረገድ በመንግስት ተወስኖ እየተገነባ ያለው የመኖሪያ ቤት ሕገወጥ ነው ብለዋል፡፡ ከሃላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የም/ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 653/2001 መኖሩን ያስታወሱት ባለሙያው፣ ይህ ሕግ ለሀገሪቱን ፕሬዚዳንት፣ ጠ/ሚኒስትር እና ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡
በአዋጁ እንደተቀመጠው እነዚህ ባለስልጣናት ከሃላፊነት ሲነሱ በስራ ላይ እያሉ የሚሰጣቸው ደመወዝና አበል እንደማይቋረጥ፣ በመንግስት ወጪ እስከ አምስት መኝታ ክፍል ያለው መኖሪያ ቤት እንደሚሰጣቸው፣ የተሸከርካሪ የቢሮ አገልግሎት እንደሚያገኙ፣ የግል ደህንነት ጥበቃ እንደሚሰጣቸው፣ ሲታመሙ በሀገር ውስጥ ወይንም በወጪ ሕክምና እንደሚያገኙ ደንግጎአል ይላሉ። ሆኖም አዋጁ ለተሰናባች ወይንም ጡረተኞች ባለስልጣናት የመዋኛ ገንዳ ያለው ቅንጡ መኖሪያ ቤት ተሰርቶ በስጦታ መልክ እንደሚሰጣቸው ጨርሶ የተገለጠ ነገር እንደሌላ ይገልጻሉ፡፡ ለሚኒስትሮች ሲሆን ደግሞ ጥቅሙ እየቀነሰ ይመጣል የሚሉት ባለሙያው፣ በአሁኑ ሰዓት ስድስት ከፍተኛ ጡረተኛ ባለስልጣናት ከ 150 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ዘመናዊ ቤት ተሰርቶ ይሰጣል የተባለው ዜና ከሕጉ አንጻር ሲመረመር ሕገወጥና እንዴትስ ሊወሰን እንደቻለ ግራ የሚያጋባ ነው ብለዋል፡፡
ሙስናና ብልሹ አሰራርን እታገላለሁ እያለ ጠዋት ማታ የሚምል መንግስት በሕግና በስርኣት ባልተቀመጠ ሁኔታ ጥቂት የመንግስት ባለስልጣናት ጡረተኞችን ከግብር ከፋዩ ሕዝብ ጉሮሮ ነጥቆ ቤት ሰርቶ ለመሸለም እየተጋ መሆኑ አሳዛኝ ነው ሲሉ መናገራቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል። ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰራው እጅግ ዘመናዊ ቤት ሲጠናቀቅ፣ ሁለተኛ ዙር የግንባታ ፕሮጀክት ለሌሎች ባለስልጣናት እንደሚጀመር መዘገቡ ይታወቃል።
በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቤታቸው ህገወጥ ነው በሚል ከፈረሰባቸው በሁዋላ አብዛኞቹ በቤት እጦት እየተሰቃዩ ነው።
በአገሪቱ 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ አሜሪካና አንዳንድ የምእራብ አገራት የእርዳታ ስንዴ መላክ ጀምረዋል። በከተሞች የሚታየው የኑሮ ውድነትም ለአብዛኛው ነዋሪ የሚቀመስ አልሆነም። በዚህ ሁሉ መሃል የመንግስት ባለስልጣናት እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የጡረታ ቤቶችን ማሰራታቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሰውተው የታገሉት በህዝብ ሃብት የራሳቸውን ዘመናዊ ኑሮ ለመኖር ነው የሚል መልእክት እንደሚሰድና ለወትሮም ብዙም ህዝባዊ ተቀባይነት ያላገኘው ሙስናን እንዋጋለን የሚለው መፈክር ጨርሶ ዋጋ እንዲያጣ የሚያደርገው ነው ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
No comments:
Post a Comment