ኢሳት ዜና :-ከሐምሌ 2007 እስከ ጥቅምት 30 /2008 ባሉት ጊዜያት ብቻ 222 ሚሊየን ዶላር ከወጭ ንግድ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 177 ሚሊየን ዶላር ያህሉን ብቻ ነው፡፡
ሀገሪቱ ወደውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች መካከል የቅባት እህሎች ጥራጥሬ፣ ቅመማቅመም፣ ቡና፣ ጫት የሚገኙበት ሲሆን በተለይ የቅባትና የጥራጥሬ እህሎት የዓለም ገበያ ዋጋ መውደቅ ጋር ተያይዞ ገቢው ሊያሽቆለቁል እንደቻለ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመልክቶአል፡፡
በሩብ ዓመቱ ከቅባት እህሎች 80 ነጥብ 57 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 50 ነጥብ 35 ሚሊየን ዶላር ነው፡፡ ከጥራጥሬ እህሎች 55 ነጥብ 16 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 48 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር መገኘቱ ተነግሮአል፡፡
የውጭ ንግድ ገቢ ባለፈው ኣመት 1 ነጥብ 42 ቢሊየን ዶላር ለማስገባት ታቅዶ 1 ነጥብ 05 ቢሊየን ዶላር ማሳካት መቻሉ የሚታወስ ነው፡፡
የወጭ ንግድ ገቢ ባለፉት አምስት ኣመታት ማሽቆልቆል የታየበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሪ ችግር እንድትዘፈቅ አድርጓል ፡፡ ይህም ሁኔታ በተለይ ለአስመጪዎች በቂ የውጭ ምንዛሪ ማዳረስ ባለመቻሉ ቅድሚያ
ለሚሰጣቸው ዘርፎች ብቻ ቅድሚያ እንዲሰጥ በማድረግ ሌሎች ዘርፎች ያለስራ እንዲቀመጡ አስገድዶአል፡፡ ይህም ሁኔታ የጥቁር ገበያን ተፈላጊነት በማሳደጉ የአንዳንድ ባንኮች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሳይቀር በሕገወጡ የጥቁር ገበያ በመሳተፍ ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
No comments:
Post a Comment