እነ የሺዋስ ለሶስተኛ ጊዜ ባልተገኙበት ቀጠሮ ተሰጠባቸው
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ከተበየነላቸው በኋላ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ዛሬ ጥቅምት 29/2008 ዓ.ም ለሶስተኛ ጊዜ ባልቀረቡበት ለህዳር 6/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ጥቅምት 17/2008 ዓ.ም፣ ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም እንዲሁም ዛሬ ጥቅምት 29/2008 ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው ለሶስተኛ ጊዜ በሌሉበት የተቀጠረባቸው አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ሀምታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሽበሺና አብሯቸው ይገብኝ የተጠየቀበት አቶ አ
ብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡
ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ማስረጃ ዝርዝር ከብይን ጋር ተያይዞ ባለመቅረቡ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ መርምሮ ለመወሰን ስላልቻለ፤ ይግባኝ ያስቀርባል አያስቀርባል የሚለውን ለመወሰን በእስር ፍርድ ቤቱ ያሉ ዝርዝር የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ተያይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ሲሆን በዛሬው ችሎት አቃቤ ህግ ማስረጃዎቼ ያላቸውን አያይዞ ቀርቧል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ ‹‹መረጃዎቹ ስላልተመረመሩ መርምሮ ይግባኝ ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለውን ለመወሰን›› በሚል ለህዳር 6/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment