Monday, January 1, 2018

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስን የደንብ ልብስ በመዝረፍ በአምቦ ከተማ ዘረፋና ድብደባ ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች መያዛቸውን የአምቦ ከተማ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታወቀ

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስን የደንብ ልብስ በመዝረፍ በአምቦ ከተማ ዘረፋና ድብደባ ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች መያዛቸውን የአምቦ ከተማ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃንም የግለሰቦቹን መያዝ በዘገባቸው ላይ አስፍረዋል። በሌላ በኩል የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ሶስቱም ዘራፊዎች የትግራይ ክልል ተወላጆች ሲሆኑ ስማቸውም ይፋ ሆኗል። አንዳንድ የፓለቲካ ተንታኞች እንደሚገምቱት ድርጊቱ ከተራ ዘረፋነቱ ይልቅ በሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት የተቀነባበረ ሊሆን ይችላል። የአምቦ ከተማ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ የሕወሃት ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና እንደዘገበው የኦሮሚያ ክልል አድማ በታኝ ፖሊሶችን ልብስ በመልበስ ዘረፋ ሲፈጽሙ የተያዙት ሶስት ግለሰቦች ናቸው። በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የዘረፋ ወንጀል ሲፈጽሙና በነዋሪው ላይ አካላዊ ጉዳት ሲያደርሱ
መቆየታቸውም በዘገባው ተመልክቷል። በተለመደው የዘረፋና የድብደባ ተግባር ሲንቀሳቀሱ ታህሳስ 19/2010 ከምሽቱ 4 ሰአት ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሶስት ግለሰቦች ሁሉም የኦሮሚያ ክልል አድማ በታኝ ፖሊስ ዩኒፎርም መልበሳቸውም ይፋ ሆኗል። የአምቦ ከተማ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው ድርጊቱ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስንና የወጣቶችን ስም ለማጠልሸት የተቀነባበረ ነው ብሎታል። በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በቁጥጥር ስር የዋሉት ሶስት ሰዎች ስለመሆናቸው ከመገለጹ ውጪ ማንነታቸው አልተጠቀሰም። ሆኖም በሌሎች ወገኖች በፎቶግራፍ ተደግፎ በተሰራጨው መረጃ በቁጥጥር ስር የዋሉት ጎይቶም በርሄ፣ገብረኪዳን ሐዱሽና ሃይሌ ፍስሃ የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል። የፖለቲካ ምሁራን ድርጊቱን በሕወሃቱ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሚመራው የደህንነት ተቋም ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረም ይገምታሉ። የአምቦ ከተማ ሕዝብ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ላይ በመማረር የፌደራል ሃይል እንደገባ የሚደረገውን ግፊት እንዲቀበል የተቀነባበረ ሳይሆን እንዳልቀረም ታምኖበታል። የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የደህንነት ሃይል ከ20 አመት በፊት በአምቦ ከተማ ደራራ ከፈኒ የተባሉ ታዋቂ ኢትዮጵያዊን በተቀነባበረ መንገድ በደህንነት ሃይል ማስገደሉ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መዘገቡን ማስታወስ ይቻላል።

No comments:

Post a Comment