በዩኒቨርስቲዎች በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ወደቤታቸው የሄዱ ተማሪዎች ጥሪ ቢደረግላቸውም መመለስ እንዳልቻሉ የመንግስት ሪፖርት አመለከተ። ሪፖርቱ እንዳመለከተው በዩኒቨርቲዎች ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ከባድ ደረጃ ላይ ይገኛል። እናም ችግሩ መፍትሄ ካላገኘ የባሰ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ሪፖርቱ ይገልጻል። በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ግጭት ተቀስቅሶ በነበረባቸው 19 ዩኒቨርስቲዎች በመዟዟር ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የመንግስት ግብረሃይል ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል። የገብረ ሃይሉ አካል የሆኑ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ሪፖርቱን መነሻ አድርገው እንደገለጹት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላትና ተማሪዎች በሀገሪቱ ባለው የፖለቲካ ቀውስ አሁንም በመታመስ ላይ ናቸው። ተማሪዎቹ በብሔር በመደራጀት እርስበርሳቸው በፍራቻ አይን እየተያዩ እንደሆነም ሪፖርቱ ያመለክታል። ይህን ስሜት መቀየር ካልተቻለም አሁን ካለው የባሰ ቀውስ በዩኒቨርቲዎች ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል በሪፖርቱ ተጠቁሟል። በግጭቱ ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱት ተማሪዎች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ወደ የተቋማቱ ለመመለስ ፍላጎት አላሳዩም ተብሏል። እንደ ሪፖርቱ ገለጻ የተማሪዎች ስጋት አሁንም ግጭት አይቀርም ከሚል ስጋት ነው። አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት ጀምረው ለተማሪዎች ጥሪ ቢያደርጉም ብዙዎቹ ተማሪዎች ለመመለስ ፍቃደኛ አይደሉም ነው የተባለው። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንደሚሉት በዩኒቨርስቲዎች ለተነሳው ግጭት ዋነኛ ምክንያት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው። በዚህ ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶችም የ4 ተማሪዎች ሕይወት እንዳለፈ አረጋግጠዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በግጭቱ የሞቱ ተማሪዎች ቁጥር ግን ከዚህ በላይ ነው። የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ በአብዛኛው ያነሷቸው ጉዳዮች በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ይደረግላቸው፣በሕዝብ ላይ የሚካሄደው ግድያ ይቁም የሚሉና ለብሔር መለያየትና ግጭት ምክንያት የሆነው የአገዛዙ ፖሊሲዎች ናቸው የሚል ነው።
No comments:
Post a Comment