የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ንብረት የሆኑ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እንዲሁም ሌሎች ኩባንያዎችን በተመለከተ ወይዘሮ አዜብ መስፍን ለሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የውስጥ ሪፖርት ከአመታት በኋላ ተጋለጠ።
በሃገሪቱ ህግ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይኖረው ይከለክላል።
ይህ ባለ 92 ገጽ ሪፖርት የሕወሃት ኩባንያዎችን ዝርዝር አፈጻጸምና ገቢያቸውን የተመለከተ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
ወይዘሮ አዜብ መስፍን ለሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ሪፖርት እስከተጻፈበት 2007 ድረስ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ ንብረት የሆኑት የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና የዜና አገልግሎት ተቋማት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ሬዲዮ ፋና የአሁኑ ፋና ቴሌቪዥን እንዲሁም ዋልታ ዜና አገልግሎትና ዋልታ ቴሌቪዥን መሆናቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ የመቀሌው ድምጸ ወያኔ ሬዲዮ እንዲሁም በሽሬና በሁመራ ተጨማሪ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች እንዳሉትም ከባለ 92ቱ ገጽ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
የሕወሃት ንብረት በሆነው ኤፈርት ሙሉ በሙሉና በከፊል የተያዙት እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከሀገሪቱ ሕግ ውጪ እንደሚንቀሳቀሱም መረዳት ተችሏል።
የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ የሆነ መገናኛ ብዙሃን እንዳይኖረው እንዲሁም በንግድ ስራ እንዳይሰማራም በሕግ የተከለከለ ነው።
ሆኖም ህጉ በሕወሃት ላይ ተፈጻሚ ባለመሆኑ በሃገሪቱ ከፍተኛው የንግድ ተቋም ባለቤትና የበርካታ ኩባንያዎች ባለንብረት የሕውሃቱ ኤፈርት መሆኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን ለግልና ለኩባንያዎች ጭምር መፍቀድ የጀመረው በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ ቢሆንም የሕወሃቱ ሬዲዮ ፋና ከህዳር 1988 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ጣቢያውን ከፍቶ ሲሰራ ቆይቷል።
አሁን በቴሌቪዥን ጭምር አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።
ከአመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ለግል ቴሌቪዥን የብሮድካስት ባለስልጣን ፈቃድ ሰጠ በተባለበት ወቅት ፍቃዱን ያገኙትም ንብረትነታቸው የሕወሃት የሆኑት ሬዲዮ ፋናና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነበሩ።
ፍቃዱን የሚሰጠው የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶምና ምክትላቸው አቶ ልኡል ገብሩም የህወሃት አባል መሆናቸው ይታወቃል።
እነዚህ ንብረትነታቸው የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሆኑት ተቋማት ማለትም ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና ሬዲዮ ፋና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደ ገንዘብ በአዲስ አበባ ከተማ ጥቁር አንበሳና ቴድሮስ አደባባይ ሕንጻ ገንብተዋል።
ጥቁር አንበሳ ፊት ለፊት የሚገኘው ባለ 10 ፎቅ የሬዲዮ ፋና ሕንጻ ሲገነባ የመረቁት ሕንጻው በተሰራበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ እንደነበሩም በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተላለፈው በምስል የተደገፈ ዘገባ ማስታወስ ይቻላል።
ንብረትነታቸው የሕወሃት መሆናቸው የሚገለጸው ኢ ኤን ኤን ቴሌቪዥና ሌሎችን በተመለከተ ወይዘሮ አዜን መስፍን ለስራ አስፈጻሚው ባቀረቡት ሪፖርት ውስጥ አልተካተተም።
ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ደግሞ ኢ ኤን ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ አለመቋቋሙም ይታወቃል። ሪፖርቱ በ2007 የቀረበ ሲሆን ኢ ኤን ኤን የተቋቋመው በ2009 ነው።
No comments:
Post a Comment