የሕወሃት ንብረት የሆነው ኢፈርት ከሁለት ኩባንያዎች ጋር በፈጠረው የሶስትዮሽ ግንኙነት አዲስ የጣራ ክዳን ፋብሪካ 2 ቢሊየን በሚጠጋ ብር ሊገነባ ነው። የኢፈርት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አዜብ መስፍን ስምምነቱን ከሲንጋፖሩ ኩባንያ ኩስቶና ፈርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ከተባሉ ኩባንያዎች ጋር ተፈራርመዋል። ፋብሪካውን በመቀሌ ወይም አቤዲ በተባሉ የትግራይ አካባቢዎች ለመገንባት የቦታ መረጣ እየተካሄደ ይገኛል። በስምምነቱ መሰረት መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሁለቱ ኩባንያዎች ጋር ተጣምሮ የ60 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል። ቀሪዎቹ 2 ኩባንያዎች ደግሞ የ40 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረው የሕዉሃቱ ኤፈርት በትግራይ የሚቋቋመው የጣራ ክዳን ፋብሪካ ምርቱን ለመኖሪያ ሕንጻዎችና ለጋራ መኖሪያ ቤቶች መገንቢያነት እንደሚያውል አስታውቋል። ፋብሪካው የጂብሰም ሰሌዳዎችና ቀለማትን ለማምረት እቅድ እንዳለውም ወ/ሮ አዜብ መስፍን ገልጸዋል። በክልሎች መካከል የልማት ልዩነቶች መፈጠራቸውን ያመነው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ግምገማ ችግሩን ለማስተካከል እንደሚሰራ መግለፁ ይታወሳል። ከሕወሃት ስራ አስፈፃሚነት የታገዱት ወ/ሮ አዜብ መስፍን አሁንም ግዙፉን የኤፈርት ኩባንያ በመምራት መሶቦ በትግራይ ለሚያስፋፋው ፋብሪካ ተጨማሪ እድል ፈጥረዋል። የኤፈርት አጠቃላይ ካፒታል 8 ቢሊየን ብር ሲሆን በስሩም ከ50 ሺህ የሚበልጡ ሰራተኞችን ያስተዳድራል። ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ንግድ ባንኮች ያለምንም የመያዣ ዋስትና በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ሳይመለስ ባክኖ መቅረቱም ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment