Tuesday, January 23, 2018

በወልድያ እና አካባቢው ያለው ውጥረት እንዳለ ነው

ዛሬ ጥር 15 ቀን 2010 ዓም ሳምንታዊው የማክሰኞ ገባያ በወጣቶች ትዕዛዝ እንዲበተን ተደርጓል። ወጣቶቹ “ የወገኖቻችን ደም ሳይደርቅ ግብይት ማድረግ አይቻልም” የሚል አቋም በመያዝ እና ወደ ገበያው በማምራት ግብይቱ እንዳይካሄድ በማድረግ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
ከወልድያ በ 20 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጎብዬ ከተማ ላይ የከተማዋ ወጣቶች ማንኛውም እቃ የጫነ ተሽከርካሪ ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል እንዳይጓዙ ከልክለው ውለዋል። ሁለት አውቶቡሶች እና አንድ ታታ የጭነት መኪና ተሰብረዋል። የተቃውሞው መነሻ የተወሰኑ የጎብዬ ወጣቶች ቆቦ ከተማ ተወስደው በወታደሮች በኤሌክትሪክ ተገርፈው መለቀቃቸውን ተከትሎ ሕዝቡ ድርጊቱን ተቃውሞ እርምጃ በመውሰዱ ነው። 
ሃራ ከተማ ላይ ደግሞ ትናንት ምሽት 2 ሞተር ሳይክሎችና አንድ ተሽከርካሪ የተቃጠለ ሲሆን፣ በከተማዋ የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 6 አድርሶታል። ከ3 ቀናት በፊት የመሶቦ ስሚንቶ ፋብሪካ ንብረት የሆኑ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው ይታወቃል።


ወኪላችን በላከልን መረጃ መሰረት በአጋዚ ወታደሮች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 12 ነው። ከሟቾች መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው። የተገደሉት ሰዎች የአገዳደል ሁኔታ ጭካኔ የተሞላበት እንደነበር ወኪላችን ገልጿል። የ9 ክፍል ተማሪ የሆነው የአቶ እሸቴ ጀመረ ልጅ የሚካኤል ታቦት በሚገባበት ጥር 12 ቀን 2010 ዓም ከቆሰላ በኋላ፣ አባቱ አቶ እሸቴ በባጃጅ መኪና ወደ ሆስፒታል ሲወስዱት አጋዚዎች መኪናውን አስቁመው “ ጨርሰው” በማለት ደረቱ ላይ በጥይት መትተው በግፍ ገድለውታል።
“አንዲት የመቻሬ ሜዳ ሴት ልጇን ልትፈልግ ወደ ከተማ በመምጣቷ፣ አጋዚዎች “ አታልፊም” ብለው ሲከለክሉ ‘ልጄን ልፈልግ’ ነው በማለቷ ግደላት የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶ በግፍ ተገድላላች።”
ገ/ መስቀል ጌታቸው የተባለው ወጣት ደግሞ ከጓደኛው ጋር ወደ ቤቱ ሲመጣ በመኪና ላይ በተጠመደ ሰናይፐር በተተኮስ ጥይት ስድስት ቦታ ላይ ተመትቶ ተገድሏል። ወጣት ገብረ መስቀልን የገደለው ኮሎኔል ዮሃንስ የተባለ ግለሰብ ሲሆን በጥቁር ቢ 8 መኪና ውስጥ ሆኖ በአልሞ ተኳሽ መኪና ተኩሶ እንደገደለው መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ወኪላችን ዘግቧል። ገ/ መስቀልን ለመቅበር የወጡ ሰዎች መቻሬ ሆቴል ፊት ለፊት ሲደርሱ አጋዚዎች አስለቃሽ ጭስ እየተኮሱ ሬሳ አያልፍም በማለታቸው ሕዝብ ተቆጥቶ በአገዛዙ ደጋፊዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። መቻሬ ሆቴል ፣አርሴማ ሆቴል ፣እንዝር የተባሉና ሌሎችንም የባለስልጣኖች ህንፃዎችንና መነሪያ ቤቶች አውድሟል ። ወኪላችን የትግራይ ሰዎች ኢላማ እንደተደረጉ ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ የሚዘገበው ስህተት ነው ይላል። የከተማው ከንቲባ ቤት የተቃጠለው ትግሬ ስለሆነ አይደለም የሚለው ወኪላችን፣ የመቻሬ ሆቴል ባለቤት የመርሳ ሰው የሆኑት አቶ አህመድ ናቸው ሲል ገልጿል። የአቶ ዳዊት በርሄ፣ ንብረቶችና ቤት እንዲወድም የተደረገው ለህወሃት ደህንነቶች መረጃ ያቀብላል በሚል ምክንያት እንደሆነ እንጅ በዘር ጥላቻ አለመሆኑን ወኪላችን ገልጿል። አቶ አባይ ጸሃዬ የአቶ ዳዊት በረሄ እናት ወንድም የአቶ ዳዊት አጎት ናቸው።
ወጣቶቹ ከክልሉ መሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት ሰራዊቱ ከወልድያ ከተማ ወጥቷል። ትናንት በነበረው ስብሰባ ላይ የተገኙት አቡነ ኤልያስ ፣ ለአቶ ገዱ “ ዘጠና ሰባት ላይ ተሸንፋችሁ በጉልበት መግዛት የጀመራችሁ ዕለት፣ ወልቃት እና ራያ የኢትዮጵያ ሳይሆን የትግራይ ነው ያላችሁ ዕለት ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን በጎሳ ክልል የከፋፈላችሁ ዕለት፣ ያፈናችሁት እሳት ነው የሚለበልባችሁ” ብለው እንደነገሩዋቸው ወኪላችን አክሎ ገልጿል። “ለማ መገርሳ ጥሩ ጀምሯል የእሱን ፈለግ ተከተሉ” ብለው እንደመከሩዋቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በወልድያ የተፈጸመውን ጥቃት ኮንኗል። ለጥቃቱ የመንግስትን የጸጥታ ሃይሎች ተጠያቂ አድርጓል። አስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል። መንግስት የፖለተካ ማሻሻያ እንደሚያደርግ በተናገረ ሁለት ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ይህን እርምጃ መውሰዱ በጣም የሚያጸጸት ነው ሲል ተመድ አስታውቋል።
ውድ ተመልካቾቻችን ትናንት በተሰራው ዜና ላይ የሃበሻ ክሊኒክ የወያኔ ንብረት እንደሆነ ተቆጥሮ መቃጠሉን የተመለከተው ዜና ስህተት መሆኑንና የተቃጠለው ሃበሻ ክሊኒክ ሳይሆን ከጎኑ ያለ የህወሃት አባል የሆነ ግለሰብ መኖሪያ ቤት መሆኑን ወኪላችን ስፍራው ድረስ በመሄድ አረጋግጧል። ኢሳት በተፈጠረው ስህተት የሃበሻ ክሊኒክ ባለቤትን ይቅርታ ይጠይቃል።

No comments:

Post a Comment