ምኒልክ ሆስፒታል እስር ላይ የሚገኙትና ህክምና የተከለከሉት አቶ በቀለ ገርባ ተገቢ ህክምና ካላገኙ አይናቸው እስከወዲያኛው ላያይ ይችላል ማለቱን ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ለቪኦኤ ገልፃለች። የደም ግፊት በሽታ ያለባቸው አቶ በቀለ ገርባ በቂሊንጦ እስር ቤት ህክና ተከልክለው ቆይተዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቶ በቀለ ገርባ ህክምና እንዲያገኙ በተደጋጋሚ ለእስር ቤቱ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም እስር ቤቱ ሳያሳክማቸው ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት የአቶ በቀለ ገርባ የግራ አይን የተጎዳ ሲሆን ህመሙ ከባሰባቸው በኋላ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ልጃቸው ለቪኦኤ ገልፃለች። የምኒልክ ሆስፒታልም አቶ በቀለ ገርባን ማከም እንደማይችል በመግለፅ ወደ ሌላ የግል የህክምና ተቋም "ሪፈር" ፅፎላቸዋል። ምኒልክ ሆስፒታል አቶ በቀለ በአግባቡ ህክምና ካላገኙ አይናቸው እስከወዲያኛው ላያይ ይችላል ሲል ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን ገልፆአል ተብሏል። አቶ በቀለ ገርባ ተገቢ ህክምና ካላገኙ አይናቸው እስከወዲያኛው ላያይ ይችላል የሚል አስደንጋጭ የባለሙያ ማስጠንቀቂያ በተሰጠበት ሁኔታ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አቶ በቀለን በግል የህክምና ተቋም አላሳክምም ማለቱን ልጃቸው ለቪኦኤ ገልፃለች።