ኢሳት (ግንቦት 7 ፥ 2009)
የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በሌሎች የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አባላት ላይ ሲሰጥ የነበረን የመጀመሪያ ዙር ብይን ለሁለተኛ ጊዜ አራዘመ።
ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ወይም በነጻ ይሰናበቱ የሚል ብይን ሰኞ ያስተላልፋል ተብሎ ቢጠበቅም ለግንቦት መጨረሻ ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ዘግቧል። አቃቤ ህግ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ አቀርበዋለሁ ያለው የቪዲዮ ማስረጃን ለፍርድ ቤቱ ባለማቅረቡ ምክንያት ሲጠበቅ የነበረው ብይን ሊሰጥ አለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ መግለጹ ታውቋል።
ይቀርባል ተብሎ የነበረው ይኸው ማስረጃ ቀርቦ ቢሆንም እንኳ ጉዳዩን ለመመልከት ጊዜ እንደሚፈጅበት ፍርድ ቤቱ አክሎ አስረድቷል።
አቶ በቀለ ገርባን ጨርሞ 22 የኦፌኮ አመራሮችና አባላት ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል። ከሳሽ አቃቤ ህግ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ህዝባዊ ተቃውሞን ቀስቅሰዋል ሲል የሽብርተኛ ወንጀል ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው።
ይሁንና የተከሳሾቹ ጠበቆችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የፍርድ ሂደቱ ፖለቲካዊ ተልዕኮ እንዳለውና ጊዜ መውሰዱን በመግለፅ ላይ ናቸው።
የኦፌኮ አመራሮቹና አባላቱ በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸምባቸው ቆይተዋል። በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ከ24ሺ የሚበልጡ ሰዎች ለእስር ተዳርገው የነበረ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከወራት እስራት በኋላ ተለቀዋል። ይሁንና ወደ አምስት ሺ አካባቢ የሚጠጉት ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ክስ እንደሚመሰረትባቸው የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የታሰሩት ሰዎች ግን መቼ ለፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የታወቀ ነገር የለም።
No comments:
Post a Comment