ኢሳት (ግንቦት 14 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ደርሶ ከነበረው አደጋ የተረፉ ሰዎች ቃል የተገባላቸው የገንዘብና መጠለያ ቤት ድጋፍ እስካሁን ድረስ እንዳልተሰጣቸው አስታወቁ። ኮንዶሚኒየም ቤቶች በስጦታ እንደተበረከተላቸው ሲገለፅ ቢቆይም፣ እነርሱ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አሁንም ከመጠለያ መውጣት አልቻሉም። ይሰጣቸው የነበረው ምግብ ከሶስት ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል። ተጎጂዎችም ለፖሊስ ሳያሳውቁ መንቀሳቀስ አይችሉም።
ከ130 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አደጋ ተከትሎ በርካታ መንግስታዊ ተቋማት የግል ባለሃብቶች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ከአደጋው የተረፉ ሰዎች መልሶ ለማቋቋም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰው እንደነበር በወቅቱ ቢገለጽም፣ የተጎጂ ቤተሰቦች በባንክ አካውንታቸው ውስጥ አንዳችም የገባ ገንዘብ አለመኖሩን ተናግረዋል። ገንዘቡ እንደገባላቸው የባንክ አካውንት ክፈቱ ተብለው አካውንት መክፈታቸውንም አስታውሰዋል።
ከዚሁ የገንዘብ ልገሳ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተወሰኑ ተጎጂዎች የመኖሪያ ቤት ቁልፍ ሲያስረክቡ በቴሌቪዥን ጣቢያ ታይተዋል።
ይሁንና አሁንም ድረስ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ከአደጋው የተረፉ ነዋሪዎች በመገናኛ ብዙሃን በኩል የቀረበው ዘገባ ተፈጻሚ አለመሆኑንና ለ54 ቤተሰቦች ቃል የተገቡት ቤቶች እስካሁን ድረስ አለመስጠታቸው ቅዳሜ ዕለት ለታተለመው ሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ ገልጸዋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚሁ ተጎጂዎች የተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የገለጹ ሲሆን፣ በቀን ሶስት ጊዜ ሲቀርብላቸው የነበረ የምግብ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ተቀንሶ በየዕለቱ ከ9 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት አንድ ላይ እንደሚመጣላቸው ተናግረዋል።
የከተማዋ አስተዳደር ቤተሰቦቻቸውን በህይወት ላጡ ተጎጂዎች 10 ሺ ብር ለቀብር ማስፈጸሚያ እንዲሁም ቤታቸውን ላጡ ሃጋዊ ተከራዮችና ባለንብረቶች ለሆኑ ቤተሰቦች የካ ክፍለ ከተማ አባዶ ኮንዶሚኒየም ሳይት የስቱዲዮ ቤት አስረክቬያለሁ ማለቱ ይታወሳል።
ይሁንና ተላልፈው ተሰጥተዋል የተባሉት ቤቶች ገና ተሰርተው እንዳልተጠናቀቁና አንድም ሰው የተረከበ አለመኖሩን ከጋዜጣው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
የገንዘብም ሆነ የመጠለያ ድጋፍ ቃል በተገባላቸው መሰረት እንዳላገኙ በመግለፅ ላይ ያሉት ተጎጂዎች 98 ያህል ተጎጂ ቤተሰቦች በጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
እነዚሁ ተጎጂዎች ገንዘብ ይሰጣል ተብለው የባንክ አካውንት እንዲከፍቱ ቢደረግም እስካሁን ድረስ የገባላቸው ገንዘብ እንደሌለ አክለው ገልጸዋል።
የከተማው አስተዳደር ህጋዊ ይዞታ ለነበራቸው 14 አባወራዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ውስጥ 175 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ቦታውን ለመረከብ ሲጠባበቁ የነበሩት ሰዎች ቦታውን እንዳልተረከቡ ተናግረዋል።
በአደጋው ስድስት ቤተሰቦቻቸውን እንዳጡና በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለስምንት አመታት ያህል እንደኖሩ የተናገሩት አቶ ተመስገን መኮንን የተባሉ ተጎጂ ቃል የተገባላቸውን ቦታ ምትክ እንዳላገኙ አስረድተዋል። ምግብ እንኳን የሚያገኙት ከጓደኞቻቸው እንደሆነም ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment